ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው

80

ሀዋሳ፣ ሰኔ 11/2014(ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየጎበኘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ከጎበኟቸው የልማት ስራዎች መካከል ግንባታው በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ አንዱ ነው።

የሀዋሳ የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ እየተገነባ ያለው በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ሲሆን፣ የግንባታ ሂደቱን የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፈጻጸሙ እንዲፋጠን አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ በመገንባት ላይ ያለውንና አፈጻጸሙ 67 በመቶ የደረሰውን የዳቦና ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

እንዲሁም ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በከተማዋ እየተገነባ ያለውን የወላይታ ሶዶ አየር ማረፍያን ጨምሮ በብላቴ እርሻ ልማትና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።