የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ405 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

5

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ405 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዬ ጋር ተፈራርመዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ለአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ ልማት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንደሚውል ተገልጿል።

በዚህም 210 ሚሊዮን ዶላሩ በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ ልማት የሚውል ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ የኮቪድ-19  ወረርሽኝን ለመከላከል እንደሚውሉ የባንኩ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዬ  ተናግረዋል።

ባንኩ እስካሁን ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት 690 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የአሁኑ ድጋፍም ለአቅም ግንባታ፣ የጤና ተቋማትን ለማጠናከር እና የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ ያግዛል ብለዋል።

በተለይ በግጭት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የኮቪድ-19 ክትባቱን ለማዳረስ የተደረገ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የኮቪድ-19 ክትባትን በጥራትና በብዛት ለማዳረስ የምታደርገውን ጥረትም የዓለም ባንክ መደገፉን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች በከርሰ ምድር ውሃ ላይ በትኩረት ቢሰራ ድርቅን ለመቋቋም እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ይህም በተለያየ ጊዜ የሚከሰተውን ድርቅን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በድርቅ በተደጋጋሚ የሚጠቁ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በኬንያ እና በሶማሊያ ላይ ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ከባንኩ የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው አሁን ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የተደረገው ድጋፍ  ኢትዮጵያ በድርቅ የሚደረሰውን ጉዳት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።