የሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ የመንገድ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ

2

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሳንሱሲ-ታጠቅ -ኬላ የመንገድ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ።

መንገዱ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አመራሮች የተጎበኘ ሲሆን የመንገዱ ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል፡፡

ቀሪ ግንባታ የሚጠይቁት የእግረኛ መንገድና የትራፊክ ምልክት ተከላዎች እየተጠናቀቁ መሆኑም ተመልክቷል።  

ለመንገዱ ግንባታ የዋለው 825 ሚሊዮን ብር ሙሉ ወጪ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት ሲሆን፤ ግንባታው በአገር በቀሉ ‘አሴር ኮንስትራክሽን’ ድርጅት በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቷል።   

መንገዱ ከ13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ሲሆን ለማጠናቀቅ አራት ዓመታትን ፈጅቷል።

መንገዱ በአማካይ ከ20 ነጥብ 5 እስከ 32 ነጥብ 5 ሜትር የጎን ስፋት ያለው በመሆኑ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን በግራና በቀኝ ማስተናገድ የሚችል ነው።   

የ’አሴር ኮንስትራክሽን’ የሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ያሬድ ቢያድግልኝ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር ቢገጥመውም ግንባታውን በጥራት ማጠናቀቅ ተችሏል።   

ድርጅቱ የመንገዱን ጥራት ለማስጠበቅ የዲዛይን ማሻሻያ ማድረጉን አመልክተው አስፓልቱ ላይ ውሃ እንዳይተኛ የተፋሰስ ግንባታ መከናወኑንም አብራርተዋል።   

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የማዕከላዊ ግንባታ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ፕሮግራም ዳይሬክተር ዑመር ሁሴን በበኩላቸው፤ የቀድሞው መንገድ ጠባብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል።

መንገዱ ሰፊ ሆኖ በመገንባቱ የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖረው ማስቻሉንም ተናግረዋል።   

“ከዚህ በፊት ከሳንሱሲ ታጠቅ ለመሄድ ሰዓታትን ይወስድ ነበር” ያሉት ዳይሬክተሩ መንገዱ ለትራፊክ ክፍት ከሆነ በኋላ በጥቂት ደቂቃ ቦታው ላይ መድረስ ተችሏል ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች የመንገዱ ግንባታ መጠናቀቅ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል።  

ከአሸዋ ሜዳ ቡራዩ አካባቢ በሹፌርነት የሚሰራው ደመቀ ለገሰ፤ የቀድሞው መንገድ በጣም ጠባብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመኪና አደጋ ሲያጋልጣቸው መቆየቱን አስታውሷል።       

አሁን ላይ መንገዱ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ያለስጋት የማሽከርከር  እድል እንደፈጠረላቸው ተናግሯል።

“መንገዱ እጅግ በጣም ቆንጆ ነው፤መቆም የለም ጊዜም ነዳጅም መቆጠብ ችለናል” ነው ያሉት።   

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ገፈርሳ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ አዱኛ መንገዱ ከመሰራቱ በፊት ጫካ ነበር፤ አሁን ግን መንደራችን ወደ ከተማነት እየተለወጠ ነው ሲሉ አክለዋል።