የዳንግላ-ጃዊ የ73 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

3

ባህርዳር፣ ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴራል መንገዶች አስተዳደር ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚያስገነባው የዳንግላ-ጃዊ የ73 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአካባቢው ሰፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ማብራራታቸው ይታወሳል።

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ምርታቸውን ከብክነት በማዳን በጥሩ ዋጋ እንዲሸጡ እንደሚያስችላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጂነር ታደገኝ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮንክሪት አስፋልት መንገዱ የስኳር ፕሮጀክቶችና ሰፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሄድበት አካባቢ እየተገነባ ያለ ነው።

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባና ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የመንገዱን ዲዛይንና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በስድስት ወራት በማጠናቀቅ ግንባታው ዘንድሮ ታህሳስ ወር ውስጥ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር፤ በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባው መንገድ በትጋት እየተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

በእንይ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ድርጅት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወጋየሁ አንለይ በበኩላቸው ግንባታው ጥራቱን ጠብቆ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገዱ ግንባታ 30 ኪሎ ሜትሩ በዳንግላ ወረዳና 43 ኪሎ ሜትር የሚሆነው ደግሞ በጃዊ ወረዳ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ በጃዊ ወረዳ የ31 ኪሎ ሜትር መንገድ ቆረጣ፣ አፈር የማንሳትና የመሙላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንገድ ፕሮጀክቱ የሚገጥሙ የወሰን ማስከበር፣ የመለዋወጫና ነዳጅ እጥረት ለማቃለል ከአካባቢው መስተዳድር፣ ከፌዴራል መንገዶች አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መካሄዱን አስታውቀዋል።

“የጃዊ ወረዳ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የሚገኝበትና ከ24 በላይ ሰፋፊ ልማት የሚያከናውኑ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩበት ነው” ያሉት ደግሞ በጃዊ ወረዳ የመንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢተው አየሁ ናቸው።

ፋብሪካው የመጀመሪያ የሙከራ ምርት እያመረተ መሆኑን አመልክተው፤ ምርቱን በፍጥነትና በብዛት ወደ ገበያ  ለማስገባት የመንገዱ ችግር እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የአኩሪ አተር፣ ለውዝ፣ ሰሊጥና ሌሎች ምርቶችን ቢሸጥም በመንገድ ችግር ምክንያት  ምርቱን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዱን አስታውቀዋል።

አዲስ እየተገነባ ያለው መንገድ የገበያ ትስስር በመፍጠር የአርሶ አደሩና የባለሀብቱን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የዳንግላ-ጃዊ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታን ለማካሄድ ግንቦት 2013 ዓ.ም የተፈረመው ስምምነት መንገዱ በሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ