የተሳሳቱ ትርክቶች ለጽንፈኝነት መጠቀሚያ እየዋሉ በመሆኑ ልሂቃን ህዝብን በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል

169

ሰኔ 10/2014/ኢዜአ/ የተሳሳቱ ትርክቶች ለጽንፈኝነት መጠቀሚያ እየዋሉ በመሆኑ ልሂቃን ህዝብን በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚካሄደው አዲስ ወግ "ከፅንፎች መሐል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ"  በሚል መሪ ሃሳብ  በፅንፈኝነት መገለጫዎችና አሉታዊ ውጤቶቻቸው ላይ ውይይት ተደርጓል።

በፖለቲካ፣ ብሔር ተኮርና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እንዲሁም የፅንፈኝነትና ስነ-ልቦናዊ ተዛምዶ ላይ ያተኮሩ የመወያያ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ፤ ፅንፈኝነትና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታን በሚመለከት ባቀረቡት ማብራሪያ ፅንፈኝነት ሁሉን አቻችለው ለመሄድ የሚሞክሩ ሰዎችን መሃል ሰፋሪና አድርባይ ብሎ የመፈረጅ ስነ-ልቦናዊ መገለጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ፅንፈኝነት መልካም ነገር የለውም ያሉት ዶክተር ምህረት ራሱን ከሌላው ጋር በማነጻጸር የበላይነትን የመቆጣጠር ስነ-ልቦናን በመፈለግ የሚፈጠር ነው።

በተለይም የእኩልነት ስነልቦናን የማይቀበሉና እኛ ልዩ ነን በሚል የሚቀነቀን እሳቤ ለጽንፈኝነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ፤ ስለብሔር ተኮርና ፖለቲካዊ ፅንፈኝነት ባቀረቡት የመወያያ ፅሁፍ  የትኛውም ፅንፈኝነት  ስሪቱ ፖለቲካዊ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም ፖለቲካዊ ፅንፈኝነት አብዛኛው ማህበረሰብ የሚያምነውን እንዳይቀበልና ሌሎችን በሃይል በማስፈራራት ዓላማውን ለማስፈፀም የሚሞከርበት መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፖለቲካዊ ፅንፈኝነት ውስጥ ውድመትን መሰረት ያደረገ እንቅሰቃሴ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ከምክንያታዊነት ወደ ስሜታዊነት ያደላል ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የአንድነት ማህበራዊ ስሪትን እየሸረሸረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ብሔር ተኮር ፅንፈኝነት በአፍሪካና በኤዥያ በስፋት እንደሚስተዋል አንስተው በተለይም ድህነት፣ የታሪክ አለመስመማት፣ በማንነት ዙሪያ የሚፈጠሩ አወዛጋቢ ትርክቶች ለብሔር ተኮር ጽንፈኝነት እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ብሔር ተኮር ፅንፈኝነት እንዲስፋፋ  የራሳቸውን አጀንዳ በህዝብ ውስጥ በጠለቀ ስሜት ለማስረጽ መሞከር፣ ብሶት፣ ስጋት መፍጠርና የተስፋ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ብሔር ተኮርና ፖለቲካዊ ፅንፈኝነት የማህበረሰቡን ማህበራዊ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አንድነት በማፍረስ ሀገርን እንደሚያጠፋ ተናግረዋል።

የባህል ጥናት ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን ተሾመ በሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ዙሪያ የመወያያ ፅሁፍ አቅርበዋል።

ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ከራስ ውጭ ያለውን ሃይማኖት መለኮታዊ እንዳልሆነ መሳል፣ መቅጣት፣ ሃይማኖታዊ ክብረበዓልን ማጣጣል፣  አዳዲስ ሀሳቦችንና ሙግቶችን አለመቀበል፣  እንዲሁም  የፖለቲካ ስርዓትን በሃይል ለማፍረስና በበላይነት ለመቆጣጠር መሞከር ይስተዋልበታል ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ፅንፈኝነት ከግለሰብ ወደ ቡድን እንደሚያድግ ገልጸው አንዱ ሌላውን ባለማወቅም ፅንፈኝነት እንደሚከሰት ገልጸዋል።

ፈረንጆቹ 2019 የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው አፍሪካ በፅንፈኝነት ምክንያት በየዓመቱ 97 ቢሊየን ዶላር ሀብት አጥታለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያም ጠንካራ የነበረውን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ በሃይማኖታዊ፣ የብሄርና ፖለቲካዊ ፅንፈኝነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ፅንፈኝነትን ከሰዎች ስነ-ልቦና ለማጥፋት ረጅም የቤት ስራ እንደሚጠይቅ የገለጹት ዶክተር ምህረት፤  ገና በእንጭጩ ለማስቀረት የችግሩን መነሻ ማወቅና ራሰን መመልከት ይገባል ብለዋል።

የፅንፈኝነት ሀሳብ አራማጅ የሆኑ መሪ ግለሰቦች ላይ በመስራት ተከታይ እንዳይኖራቸው ማድረግና አብዛኛውን ሰው ከችግሩ ለመታደግ መስራትም ሌላኛው መፍትሄ ነው።

ፕሮፌሰር ጄይላን በበኩላቸው በየዘውጉ የሚታዩ የፅንፈኝነት ችግሮችን በመቅረፍ ሰላሟ የተረጋገጠና ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ወደ ወርቃማው መሐል መምጣት ተገቢ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ልሂቃን ብሔር ተኮርና የፖለቲካ ፅንፍ የሚጠፍሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ማህበራዊ ስሪት ለማስቀጠል መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

ዶክተር ሰለሞን የሃይማኖቶችመሪዎችናተከታዮችመካከል ውይይትና ቅርርብን መፍጠር እንደሚገባቸውገልጸው፣ መንግስት ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት እንደ ብሔር ፅንፈኝነት ሀገርን ለአደጋ እንዳያጋልጣት እንዲሰራ ጠይቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም