በተማሪዎችና መምህራን እየተሰሩ ያሉ የሳይንስ ፈጠራ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው ነው

95

ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተማሪዎችና መምህራን እየተሰሩ ያሉ የሳይንስ ፈጠራ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

“የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዟችንን በሳይንስ ፈጠራ ሥራ እውን እናደርጋለን!” በሚል መሪ ሃሳብ 7ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስና የፈጠራ አውደ-ርዕይ በወዳጅነት ፓርክ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በተማሪዎችና መምህራን እየተሰሩ ያሉ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ በሌብነትና ዝርፊያ የሚባክነውን የሕዝብ ሃብት ለልማት ለማዋል የሳይንስና የፈጠራ ውጤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአውደ-ርዕዩ በተማሪዎችና በመምህራን የቀረቡት የሳይንስ ፈጠራ ሥራዎች የማኅበረሰብ ችግሮችን  በተግባር መፍታት እንደሚቻል ያሳዩበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ፤ በአውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡት የሳይንስ ፈጠራ ውጤቶች ችግር ፈቺና ለአገር ልማት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በመማር ማስተማር ሂደት በንድፈ-ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ለመቀየርና የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎች የሚበረታቱበት አሰራር በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትምህርት ቢሮው በሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች የዳበሩ ተማሪዎችን ለማብቃት ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን  ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በአውደ-ርዕዩ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች እንደየክፍል ደረጃቸው በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚያቀርቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም