በጥብቅ ደኑ ላይ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

76

ደሴ፣ ሰኔ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ "ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ላይ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የወረዳው አካባቢና ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ኃላፊ ወይዘሮ ዚነት መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ጀምሮ በጥብቅ ደኑ ላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል።

የእሳት አደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሆነ ገልጸው፤ አንድ ግለሰብ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል።

የእሳት አደጋው እንዳይዛመትና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የተለያዩ አካላት ቅንጅት ፈጥረው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረው፤ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።

አካባቢው ተራራማ ከመሆኑ ባለፈ በአሁኑ ወቅት ሀይለኛ ንፋስ በመኖሩ እሳቱ እየተስፋፋ ቢሆንም ህብረተሰቡ ጭምር በነቂስ ወጥቶ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

"ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ከ8 ሄክታር መሬት በላይ ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡ የተለያዩ እንሰሳትና አዋፋትን ጨምሮ ሀገር በቀል ዛፎች እንዳሉትም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም