በትምህርት ስርአቱ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

434

ሰኔ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የትምህርት ስርአት ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አዲስ ከተመደቡት የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤በትምህርት ስርአቱ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዘርፉ የአምስት አመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ማረጋገጥ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ለዚህ መሳካት አጠቃላይ የማህበረሰቡና የትምህርት ተቋማት ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው አዲስ የተመደቡት የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የቦርድ አመራሮቹ በበኩላቸው በሚኒስቴሩ የተጀመረው የሪፎርም ስራ እንዲሳካ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም የሙስና እና ብልሹ አሰራሮች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት የጋራ ጥረት ይጠይቀናል ብለዋል።

የትምህርት ተቋማት የእውቀት ማእከላት እንጂ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያዎች መሆን ስለሌለባቸው ለዚህም በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቀናል ነው ያሉት።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆኑ ብቁ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሁራን መፍለቂያዎች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዲስ የስራ አመራር የቦርድ አባላት መመደባቸው ለተጀመረው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮች ጋር የተደረገው የውይይት መድረክም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሀንስ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚነሱ አበይት ችግሮች መካከል የትምህርት ጥራት ዋነኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ለትምህርት ጥራት ስኬት ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተገቢና በቂ ትምህርት እያገኙ እንዲያድጉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም