የጎርፍ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ስራዎችን እየሰራሁ ነው- ባለስልጣኑ

2

ሰኔ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ መጪው ክረምት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ አደጋ እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተራራማ አካባቢዎች በከፍተኛ ጉልበት እና ፍጥነት የሚመጣው ጎርፍ በመንገዶች ላይ አደጋ እየፈጠሩ።  

ስለሆነም ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት መንገዶችን ከጎርፍ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡  

ክረምት ከመግባቱ ቀደም ብሎ በተሰሩ ስራዎች ብልሽት ያጋጠማቸው መንገዶችና ድልድዮች የመጠገን እና በቆሻሻ የተደፈኑትን የውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎችን የማፅዳት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ባለፉት 11 ወራት 320 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን የማጽዳት ስራዎች መከናወኑን አንስተዋል፡፡

አቶ እያሱ አክለውም የተሰራው የቅድመ-መከላከል ስራ ጎርፍ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የመንገድ ደህንነት የምናስጠብቅበት ሂደት ነው ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ወደ 41 የሚደርሱ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት 15ቱ መፍትሄ የተሰጣቸው ሲሆን ወደ 11 የሚሆኑ ቦታዎች በቀጣይ 2 ሳምንታት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ግንቦት 28 ቀን 2014 ዘነበወርቅ አካባቢ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ማጋጠማቸውን አንስተው ለዚህም ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የመንገድ ደህንነት ከማረጋገጥ አንፃር ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ አንስተው ደረቅ ቆሻሻዎችን በድሬኔጅ የመጨመር የግንባታ ቁሳቁስና ተረፈ ምርት መንገድ ዳርቻ እና የእግረኛ መንገድ ላይ አስቀምጦ ግንባታ ማከናወንን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

ህብረተሰቡም ሆነ አንዳንድ ድርጅቶች ቆሻሻን በፍሳሽ ማስወገጃዎች ውስጥ ከመጣል በመታቀብ፣ የሽንት ቤት ፍሳሾችን ከድሬኔጅ መስመር ጋር ከማገናኘት በመቆጠብ እና በቆሻሻና በደለል የተደፈኑትንም በማፅዳት ከጎርፍ አደጋ በመከላከል የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

እንዲሁም ህብረተሰቡ ህገ-ወጦችን በመከላከል በኩል ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።