የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት እና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች የገርጂ መኖሪያ መንደርን ጎበኙ

2

ሰኔ 5/2014 /ኢዜአ/ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት እና የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ የተመረቀውን የገርጂ መኖሪያ መንደር ጎበኙ ፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝቱን ያካሄዱት የፓርቲውን ያለፉት 10 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት  ግምገማ መድረክን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡

አመራሮቹ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በጉብኝታቸው የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማከናወን እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በጥራት ማከናወን የገዥው ፓርቲ ብልጽግና አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በተለያዩ አከባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የገርጂ መኖሪያ ቤት ግንባታ ቴክኖሎጂን ከፕሮጀክት አመራር ብቃት ጋር በማጣመር በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት መፍታት እንደሚቻል ያመላከተ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

ፕሮጀክቱ በመዲናዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሚሆንም እንዲሁ፡፡

ከዚህ አኳያ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ በጉብኝቱ ያገኙትን ልምድ በማካፈል መንግስት የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙም አረጋግጠዋል፡፡

በገርጂ መኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት “አልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ” የተሰኘ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ያዋለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች ቴክኖሎጂውን በማላመድ ግንባታውን በፍጥነት ያከናወኑበት መሆኑም ተገልጿል፡፡

ቴክኖሎጂው የግንባታ ጥራትና ፍጥነትን የሚያቀላጠፍ ሲሆን፤ በዚህም አስር ወለል ያላቸው 16 ህንጻዎችን በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ማጠናቀቅ ተችሏል።