ለአብሮነት እና ለኢትዮጵያዊነት ትኩረት በመስጠት ልዩነትን ማጥበብ ይገባል—ምሁራን

4

ሆሳዕና ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) አብሮነትን እና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ልዩነቶችን ማጥበብ እንደሚገባ የዋቸሞ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

“ባለፉት ዓመታት የአብሮነት ተምሳሌት የሆነው ኢትዮጵያዊነት ትኩረት አለማግኘቱ በዜጎች መካከል ለግጭት መንስኤ የሆኑ ልዩነቶች እንዲሰፉ አድርጓል” ሲሉ ምሁራኑ ተናግረዋል።   

ምሁራኑ ኢትዮጵያዊነትን ከብሔር አስተሳሰብ ማስቀደም ከተቻለ በዜጎች መካከል ልዩነቶችን በማጥበብ ሰላምን በዘላቂነት ማምጣት ይቻላል ብለዋል ።

በወራቤ የኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊና የፌዴራሊዝምና የአካባቢ መንግስት ትምህርት መምህር አባስ ሉባኔ፣ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር በነበረው አስተዳደራዊ ስርዓት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ለብሔር የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ሲቀነቀን መቆየቱን አስታውሰዋል።

“የብሔር ማንነትንና ኢትዮጵያዊነትን ማመጣጠን መቻል የግድ ይለናል” ያሉት ምሁሩ፣ የፌዴራሊዝም ስርዓትን ተግባራዊ ካደረጉ ሀገራት የተሻለ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የብሔር ማንነትንና ኢትዮጵያዊነትን ማመጣጠን ከተቻለ ግጭቶችን ማርገብ እንደሚቻል ገለጸው፣ “ሀገራዊ አንድነት እንዲመጣ ከመንግስት በተጨማሪ ሁላችንም አስተዋጾ ማድረግ አለብን” ብለዋል።     

እንደ መምህር አባስ ገለጻ ባለፉት ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች ዋልታና የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ በሆነው ኢትዮጵያዊነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አልተሰራም።

“ይህም ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ልዩነቶች እንዲስፋፉ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

መንግስትና ህዝቡ ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ከፍታና አብሮነት በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንዳለባቸው አስገነዝበዋል።

ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከፍ ለሚያደርጉ የስነ ዜጋና የታሪክ ትምህርቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር አበራ ሄቢሶ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥ የመንግስት ሀላፊነት ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

“ጠንካራ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት ሰላም እንዲመጣ ዜጎችም የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ የድርሻችንን መወጣት አለብን” ብለዋል።

“ኢትዮጵያዊያን አብሮነትን በማጠናከር የሀገርና የህዝብ ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረስ አለብን” ሲሉም ነው ምሁሩ የተናገሩት።

መምህር አበራ እንዳሉት “የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት የአንድነት የልህቀት ማዕከላትን ማደራጀት ያስፈልጋል።”

“ልዩነትን የሚያሰፉ ጉዳዮችን እንዲፈቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ድጋፍ ማድረግ ይገባናል” ያሉት አቶ አበራ፣ “የዜጎችን አብሮነት የማጠናከሩ ሥራን ለመንግስት ብቻ መተው የለብንም” ብለዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የአብሮነትን ጠቀሜታ ለተማሪዎቻችን ከማስረጽ ባለፈ እውነተኛ ታሪክ የሚያውቅ ትውልድ መፈጠር ይኖርብናል ብለዋል።