የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጀመረውን የበጎ አድራጎት ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል

65
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እያደረገ ያለውን የበጎ አድራጎት ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ሰራተኞችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክተው በመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 20 ባለ40 ኢንች ፍላት ቴሌቭዥን እና የምሳ ማብላት ፕሮግራም በዛሬው ዕለት አካሂደዋል። በዚህ ወቅት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት ፤ ሰላማዊ ፣ ውብና አስደሳች የሆነውን የዘንድሮ አዲስ ዓመት ሲከበር የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን የበለጠ በማጎልበት መሆን አለበት። ''በተለይ በአንድ ወቅት አገርን በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ያገለገሉትን አረጋዊያንን መንከባከብ ለቤተሰቦቻቸው ተስፋ ብቻ ሳይሆን አገርም ቀጣይ እንድትሆን ያደርጋል'' ብለዋል። ሚኒስቴሩ ያደረገው የቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ድጋፍ በቀጣይም አረጋዊያኑን በሚጠቅምና ለእነሱ ምቹ በሆኑ የቴክኖሎጂ ግብዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። የመቄዶኒያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩሉ ለተደረገላቸው የቁሳቁስ ድጋፍና የምሳ ማብላት ፕሮግራም ምስጋና አቅርበው ተግባሩ ለሌላው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና ተቋማት አርአያ የሚሆን እንደሆነ ገልጸዋል። ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ የሚሆነው ከገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ሁሉም ሰው አረጋዊያንን በመጎብኘትም ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይ ማዕከሉ በቀጣይ 2ሺህ ሰዎችን ተቀብሎ ለመንከባከብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ሰው ባለው ጊዜ ፍቅርና አለው ባይነትን ለአረጋዊያኑ ለመስጠት የጉብኝት ፕሮግራም አውጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል። በ2002 ዓ.ም የተመሰረተው መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአህምሮ ህሙማን መርጃ በአሁኑ ሰዓት 1ሺህ700 ሰዎችን ተቀብሎ እንክብካቤ እየሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም