በጋምቤላ ክልል በጊሎ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ

78
ጋምቤላ ግንቦት 10/2010 በጋምቤላ ክልል የአኮቦ ወረዳን ከሌሎች ተጎራባች ወረዳዎች ጋር እንዲያገናኝ በጊሎ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ትናንት ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ። ከ40 ሜትር በላይ ርዝምት ያለው ይኸው ድልድይ የተገነባው በክልሉ መንግስትና በመከላከያ ሚኒስቴር የምህንድስና መምሪያ የጋራ ትብብር እንደሆነም ተገልጿል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት በምረቃ ስነ- ስርዓት ላይ እንደተናገሩት የአኮቦ ወረዳን ከሁለት ከፍሎ በሚያልፈው የጊሎ ወንዝ ላይ ቀደም ሲል ድልድይ ባለመሰራቱ  የአካባቢው ህዝብ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳረጎ ቆይቷል። የወረዳው ህዝብ የመሰረተ ልማት አውታሮች ተጠቃሚ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከግማሾቹ የወረዳው ቀበሌዎችና አጎራባች ወረዳዎች ጋር ሊኖረው ከሚገባ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ተገድቦ መቆየቱን ገልጸዋል። ''በአሁኑ ወቅት ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት የሆነው ድልድይ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማደረግ ያስችላል'' ብለዋል። የመከላከያ ሚኒስቴር የሀገርን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ በልማት ስራ በመሳተፍ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊ ልማት እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል። በመከላከያ ስራዊት የምዕራብ ዕዝ የ12ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጀንራል ብርሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው እንዳሉት የሀገር መከላከያ ስራዊት የሀገር ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባለፍ በሀገሪቱ ለተጀመሩ የልማት ስራዎች መሳካት የበኩሉን እየተወጣ ነው። በአሁኑ ወቅትም በጋምቤላ ክልል በተለይም በጠረፋማ ወረዳዎች ያለውን የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማት አውታሮች ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ከክልሉ መንግስት በጋራ በመተባበር በዕለቱ የተመረቀውን ጨምሮ የሁለት ድልድዮች ግንባታ ማካሄዱን ተናግረዋል። ድልድዩ በአካባቢው ጸጥታን ለማስጠበቅም ሆነ የልማት ስራዎችን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመው ስራዊቱ በቀጣይ በክልሉ የጀመረውን የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ከተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ጆን ዩንግ በሰጡት አሰተያየት በጊሎ ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመሰራቱ ለዘመናት ለተለያዩ ችግሮች ተዳረገው መቆየታቸውን ተናግረዋል። በጊሎ ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመኖሩ ከወንዙ ማዶ ካሉት ዘመዶቻችን ለመገናኘትም ሆነ ግብይት ለማካሄድ ስንቸገር ቆይተናል '' ያሉት ደግሞ ሌላዋ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የታደሙት ወይዘሮ ሜሪ ኘአክ ናቸው። አሁን የተሰራው ድልድይ ችግሩን እንደሚያስወግድላቸው ተናግረዋል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት የሆነው ይኸው ድልድይ ከ40 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሲሆን ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ከመከላከያ ሚኒስቴር የምህንድሳ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም