የሲሚንቶ ሽያጭ በመንግስትና በፋብሪካዎች በሚቋቋሙ የሽያጭ ዴፖዎች እንዲሆን ተወሰነ

4

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ መንግስት በሲሚንቶ ግብይት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሲሚንቶ ሽያጭ በክልሎችና በፋብሪካዎች በሚቋቋሙ ማዕከላት እንዲከናወን ወስኗል።

የግብይት ስርዓቱ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታትም አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎችን በጊዜያዊነት አግዷል።


የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፤ ጉዳዩን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መንግስት የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ለተጠቃሚው በቀጥታ የሚሸጡበት ዲፖ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች  እንዲከፈት መወሰኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የግንባታ ስራዎች መስፋፋታቸው የሲሚንቶ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀው ይህም የግብአት  አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም እያስከተለ ይገኛል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ዘርፉን ለሲሚንቶ ግብይት ምዝበራ እና ጥቂት ግለሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ፈጥሯል ሲሉ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን በስራ ላይ ካሉ 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከል 12 የሚሆኑት ከ50 በመቶ በታች ምርት እያመረቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የማምረት አቅም የአጠቃቀም ችግር እንዲሁም ውጫዊና እና ውስጣዊ ችግሮች ፋብሪካዎቹን ለዝቅተኛ የማመረት ሂደት እንደዳረጓቸውም አብራርተዋል።

መንግስት በሲሚንቶ ምርትና ስርጭት የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ቢገኝም አሁንም ብዙ ስራ ይቀራል ነው ያሉት።

በሲሚንቶ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ መጠነ ሰፊ ህገ ወጥ አሰራሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

በግብይቱ  ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት እና የፍላጎት አለመጣጣም ለመፍታት የአጭር እና የረጅም ጊዜ መፍትሄ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል፡፡

በአጭር ጊዜም ግዙፍ የፌደራል እና የክልል የመንግስት ፕሮጀክቶች ሲሚንቶን በቀጥታ  ከፋብሪካ የሚገዙበት አሰራር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር በመሆን የሲሚንቶ መሸጫ ዲፖዎች እንደሚያዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የሲሚንቶ ምርት ፈላጊዎች በክልሎች በሚዘጋጀው መሸጫ ቦታ እንደሚገዙ በመጠቆም የሲሚንቶ ቸርቻሪዎች እና አከፋፋዮች በጊዜያዊነት ከሲሚንቶ ግብይት ውጪ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

በተጨማሪም ፋብሪካዎች ከ50 በመቶ በታች እንዲያመርቱ ያደረጓቸውን ችግሮች በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ እንዲፈቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም ሲጠናከርና ችግሩ በዘላቂነት ሲፈታ ቸርቻሪዎች እና አከፋፋዮች ከፋብሪካዎች ጋር በቀጥታ እንደሚገናኙና የቀደመው የሲሚንቶ ንግድ ስርአቱ ወደ ቦታው እንደሚመለስ ነው የጠቆሙት።

የወጣው አሰራር ከሁለት እስከ ሶስት ወራት የሚቆይ መሆኑን ጠቁመው አተገባበሩን በሚመለከት በቅርቡ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል ብለዋል።