በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው

119

ባህር ዳር ሰኔ 03/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር የተቀናጀ ጥረት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢንስቲትዩቱ የወባ ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክረምቱ መግቢያ ወቅት በተከሰተው ሙቀትና የዝናብ መቆራረጥ የወባ በሽታ ስርጭት እያገረሸ ነው።

"በዚህም ማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የወባ በሽታ በስፋት ተከስቷል" ብለዋል።

ባለፉት 11 ወራት 473 ሺህ 650 የሚጠጉ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡንና ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

ከታካሚዎቹ መካከል ከ15 ሺህ 220 በላይ ታማሚዎች ባለፈው 1 ሳምንት በበሽታው የተያዙ መሆናቸውን አቶ ዳምጤ ተናግረዋል።

"በሳምንቱ የተመዘገበው የወባ በሽታ ሪፖርት ከቀዳሚው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር የ12 በመቶ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 50 በመቶ ብልጫ አለው፤ ይህም የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል" ብለዋል።

ችግሩን ለመከላከል የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ለጤና ባለሙያዎች የሥራ ስምሪት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን የመድፈንና የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ፒ.ኤስ.ኤም ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከ400 ሺህ በላይ አጎበር ለወረዳዎች መሰራጨቱን ነው ያመለከቱት።

በመንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ትብብር የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በቆላማና አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና የአካባቢ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የተከሰተው የወባ ስርጭት በጋራ እንዲከላከሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም