የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል---ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

75
ነቀምቴ ጶግሜ 5/2010 የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር የክልሉንና  የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማጎልበት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንዳሚገባ የኦሮሚያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አሳሰቡ። ከምስራቅ ወለጋ ዞን የተወጣጡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በነቀምቴ ከተማ ተወያይተዋል በዚህ ወቅት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደተናገሩት የዴሞኪራሲ ስርዓት በመገንባት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም ለማጠናከር  በየደረጃው የሚገኙ የሀዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና የጎላ ነው። ሰላም፣ፍቅር፣የይቅርታ፣የመደመርና የአንድነት ጉዞን ለማጎልበት ባለሙያዎቹ  ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለመንግስትና ለህብረተሰቡ በማዳረስ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ዶክተር ነገሪ እንዳሉት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትን ከፍተቶቻቸውን እንዲያስተካክለሉ በማረም ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የጸዳ የህብረተሰቡ አገልጋይነታቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቦጋለ ሹማ በበኩላቸው የህዝብ ግንኙነት ተግባር ትናንትና በነበረው መንገድ የሚሰራ ሳይሆን ጥበብ በተሞላበትና የተገኘውን ለውጥ ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ " ችግር ከመፈጠሩ በፊት ከህዝቡ የሚነሳውን ጥያቄዎችና ሐሳቦች ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የመፍትሔ አቅጣጫ ማፈላለግ ይኖርበታል" ብለዋል። በውይይቱ ከተሳተፉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ፓስተር ተስፋዬ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት የተገኘው ለውጥ እንዳይቀለበስ ህብረተሰቡን በማስተባበርም ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊ ቄስ አስፋው ተርፋሳ በበኩላቸው ከዚህን ቀደም የነበረው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን  በአይን ለማየት ቀርቶ በጆሮ ለመስማት እንኳ የማይፈለግ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን የእርቅ፣የመደመርና የፍቅር ጉዞ ከተጀመረ ወዲህ መገናኛ ብዙሃን  የሕዝቡን ድምጽ እየሆኑ መምጣታቸው እንደሚበረታታ  አመልክተዋል። መገናኛ ብዙሃን  ቀደም ሲል ወገንተኝነትና ለአንድ ድርጅት የቆመ ይመስሉ  የነበሩት አሁን የህብረተሰቡን ችግርና ጥያቄ ለመመለስ መነሳሳታቸው የሚያስደስት እንደሆነ  የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር ዓለምፀሐይ ተስፋዬ ናቸው፡፡ የልማት ስራዎች ለህብረተሰቡ ከማስተዋወቅ አኳያ የህዝብ ግንኙነትና የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች ሚና ዝቅተኛ ከነበሩበት በመውጣት ለውጡን ማጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም