የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ያረጋገጠ ነው

105

ሰኔ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ያረጋገጠ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ታሪካዊና በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጭምር የተጠናከረ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ብሎም ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ስለመሆኑም ነው ያነሱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ስለመግለጻቸውም ነው ቃል አቀባዩ ያነሱት፡፡

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ፣ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት መንግስት ለሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትና ሰላም መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ማብራራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት አሁንም ለሌላ ጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በመገንዘብ በግልጽ ሊያወግዘው እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለባለስልጣናቱ መግለጻቸውንም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

የሀገራቱ ልዑካንና ባለስልጣናት በበኩላቸው መንግስት ለሰላም የሰጠውን ትኩረት አድንቀው፤ በተለይ ሀገራዊ ምክክር ለማከናወን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መናገራቸውን አምባሳደር ዲና አውስተዋል፡፡

በሌላ ዜና በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም