ግብርናው በዘላቂ ልማት ግቦች የተቀመጠለትን ዓላማ እንዲያሳካ በንግድና ስርዓተ ፆታ ላይ ማተኮር ይገባል

74
አዲስ አበባ ጶግሜ 5/2010 አፍሪካውያን ግብርናው በዘላቂ ልማት ግቦች የተቀመጠለትን ግብ እንዲያሳካ በንግድና ስርዓተ ፆታ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሓፊ ቬራ ሶንግዌ ገለጹ። በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው 'የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ፎረም' ተጠናቋል። የኮሚሽኑ ዋና ጸሓፊ ቬራ ሶንግዌ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ አፍሪካ ከዓለም ከፍተኛውን የምግብ እህል ለገበያ ማቅረብ የሚችል አቅም አላት። ይሁን እንጂ የኮሚሽኑ ጥናት እንደሚያሳየው በ 2016 ለምግብ ብቻ ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተደርጓል፤ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም አሃዙ በ 2025 ወደ 110 ቢሊዮን ዶላር ሊያሻቅብ ይችላል። በመሆኑም አፍሪካውያን በ 2030  አንድ ትሪሊዮን ዶላር የግብርና ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስቀመጡትን ግብ ለማሳካት ዝቅተኛና መካከለኛ አርሶ አደሮችን ቀጣይነት ባለው መንገድ መደገፍ አለባቸው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ መንግስታት ለስርዓተ ፆታ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ለማክሮኢኮኖሚ ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የግብርና ምርቶችን ለውጭ ንግድ ለማቅረብ ትልቅ አቅም ያለውና መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑንም አስገንዝበዋል። ይሁን እንጂ በአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ያለው ድርሻ ከ 17 በመቶ ስለማይበልጥ በአግባቡ ለመጠቀም የመሰረተ ልማትና ሎጂስቲክስ ስራዎችን ማጠናከር እንዲሁም ህገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር ይገባል ብለዋል። በአፍሪካ የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብት ለአፍሪካ ግብርና ዘርፍ እድገት ያለው ሚና የጎላ በመሆኑም መብታቸው መከበር እንዳለበት ጠቁመዋል። በአፍሪካ ግብርና በጉልበት ስራ የሚሳተፉ ሴቶች ድርሻ 45 በመቶ ቢሆንም ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ውጤታማዎቹ 30 በመቶ ብቻ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ዝቅተኛ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናቸው ነው ብለዋል፤ በዘርፉ ሩዋንዳ የተሻለ ተሞክሮ እንዳላት በማውሳት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም