በአማራና ሱማሌ ክልሎች ለ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሕዝብ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ይሰጣል

408

ባህር ዳር/ጅግጅጋ ሰኔ 2/2014(ኢዜአ). በአማራና ሱማሌ ክልሎች ለ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሕዝብ የሚሰጠው 3ኛው ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ዛሬ ተጀምሯል።

በባህርዳር በተጀመረው የክትባት ዘመቻ የክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ በክልሉ ለ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ይሰጣል።

ክትባቱ በመደበኛነት በሁሉም የክልሉ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ በተጨማሪም ህዝብ በሚበዘባቸው እንደ ማረሚያ ቤቶችና የስደተኞች ካምፖችም ለመስጠት ተንቀሳቃሽ ቡድን ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ በሽታውን የመከላከያ መንገዶችን ከመተግበር ባሻገር ክትባቱን በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ገዳይ ከሆነው ኮቪድ 19 እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ሰይድ በበኩላቸው የልብ፣ የአስምና ደም መርጋት ህመምተኛ ቢሆኑም፤ ዛሬ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የማጠናከሪያ ክትባት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

"ስለ ክትባቱ በአንዳንድ ሰዎች የሚነገረው አፍራሽ ተግባር አግባብ አለመሆኑን እኔ ራሴ ምሰክር ነኝ" ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ ኅብረተሰቡ ክትባቱን  በመከተብ ጤንነቱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

በተመሳሳይ በሱማሌ ክልል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ለመከተብ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሙድ መሐመድ አስታውቀዋል።

ምክትል ኃላፊው በጅግጅጋ በተካሄድ በ3ኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ክትባቱን ለመስጠት ከ3 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።

በክልሉ 16 ዞኖችና ስድስት ከተሞች ለሚካሄደው ዘመቻ በቂ የሰው ኃይልና የህክምና ቁሳቁስ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለአሥር ቀናት በሚቆየው ዘመቻ ከ12 ዓመት እድሜ በላይ እስከ 65 ዕድሜ ክልል የሚገኙና በተለይ በ1ኛና በ2ኛ ዙሮች ያልተከተቡ ሰዎችን ለመድረስ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ ክትባቱን በመውሰድ በሽታን የመከላከል እቅሙን እንዲያሳድግም ኃላፊው አሳስበዋል።

በክልሉ በሁለት ዙሮች በተካሄደው የክትባት መርሃ ግብር 2 ነጥብ 1ሚሊዮን ሰዎች መከተባቸውን አስታውሰዋል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ሼህ መሐመድ አህመድ ሕዝቡ ክትባቱን በመውሰድ በሽታውን እንዲከላከል አስገንዝበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የጤና ጉዳዮች አማካሪ አቶ አብዱራህማን ሹክሪ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ክትባቱ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም