በሀዋሳ የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው የዋጋ ንረቱን ያረግበዋል- ሸማቾች

157

ሀዋሳ ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ... በሀዋሳ ከተማ የግብርና ምርቶች በማህበራትና በአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ አንደሚያስችል ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች ገለጹ።

የከተማዋ አስተዳደሩ በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች የግብርና ምርቶች በቀጣይነት እንደሚቀርብ መግለጹም ተመላክቷል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ምትኩ እሸቱ እንዳሉት የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ለከተማ ግብርና የተሰጠው ትኩረት ማደግ አለበት።

ገበያውን ለማርገብም ለዕለት ከዕለት ፍጆታ የሚያገለግሉ የግብርና ምርቶችን ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉም ህዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል” ብለዋል።

ምርቶቹ በቅርበት መገኘታቸው ወደ ገበያ ሄዶ ለመግዛት የሚያወጣውን የትራንስፖርት ወጪ ከማቃለል ባለፈ፣ ትኩስ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጥረቱ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

ሌላዋ ገበያተኛ ወይዘሮ ዘሪቱ ሄርቀሎ በበኩላቸው  በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በተደራጁት ገበያዎች መገበያየታቸው ምርቶቹን በቅናሽ ለመግዛት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ገበያ ላይ ካለው ዋጋ አንጻር ሲታይ ከአምስት እስከ 10 ብር ቅናሽ እንዳለው በማመላከት።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በከተማው የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በተመረጡ ስድስት ስፍራዎች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደተጀመረ ገልጸዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎችም የፍጆታ ምርቶችን ወደ ከተማው በማስመጣት ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚሸጡባቸውን ስፍራዎች በማዘጋጀት  ድንኳን ሳይቀር ተከራይቶ ለህዝብ እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።

ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመክበር ምርት የሚደብቁና ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ከንቲባው ጠቁመዋል።

በሀዋሳ የተለያዩ አካባቢዎች በማህበራትና በአርሶ አደሮች እየቀረቡ ካሉት ከጓሮ አትክልትና የግብርና ምርቶች በተጨማሪ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ተመልክቷል።

መንግሥት ኅብረተሰቡ ያለውን ቦታ በማልማት የከተማ ግብርና እንዲያስፋፋ በማበረታታት ላይ መሆኑ ይታወቃል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም