በመዲናዋ 160 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረዋል

131

ሰኔ2/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ በ2014 በጀት ዓመት 160 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውን የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው "የኢንተርፕራይዝ ሽግግር፣ ለኢንዱስትሪ መሠረት" በሚል መሪ ኃሳብ ለ11ኛ ዙር የኢንተርፕራይዞች የምረቃ መርሃ ግብር ዛሬ አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊና ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት 10 ዙሮች 1 ሺህ 456 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።

በ2014 በጀት ዓመት ከመንግሥት የተደረገላቸውን ድጋፍ በአግባቡ የተጠቀሙና ጠንክረው የሠሩ169 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ መካከለኛ ኢንዱስቱሪ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የተሻለ ካፒታልና የሥራ ዕድል የፈጠሩ ውጤታማ ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

መንግሥት ኢንተርፕራይዞችን ስኬታማ ለማድረግ አሰራሮች በማሻሻልና ለዘርፋ አንቀሳቃሾች ድጋፍ በመሥጠት ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም ዘርፉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና ነባርና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ ትኩረት መደረጉን ነው የተናገሩት።  

ወደ መካከለኛ ኢንደስትሪ የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች ልፋታቸው ፍሬ እንዲያፈራ፣ በድካማቸው እራሳቸውን ከመቀየር ባለፈ ለአገራቸው ብልጽግና የሚተርፍ ሥራ ለመሥራት እንዲተጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም