በአዲሱ አመት የትራፊክ አደጋን ከህብረተሰቡ ጋር በመስራት እንቀንሳለን...የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

63
መቀሌ  ጳግሜ  5/2010 በትግራይ ክልል በአዲሱ ዓመት ለትራፊክ አደጋ አጋላጭ የሆኑ ችግሮችን ለመቀነስ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን  አስታወቀ። በተጠናቀቀው አመት በክልሉ በትራፊክ አደጋ ምክንያት 370 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ በኮሚሽኑ የትራፊክ አደጋ መከላከል የስራ ሂደት ባለቤት ረዳት ኮሚሽነር ገብረኪዳን ኪዳኑ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው ዓመት በክልሉ 1ሺ400 የትራፊክ አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡ በአደጋውም 370 ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን አንድ ሺህ 400 ሰዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል መዳረጋቸውን ገልጸው በንብረት ላይ ደግሞ ከ47 ሚልዮን ብር በላይ  ውድመት መድረሱን ጠቁመዋል። ይህም ከቀዳሚው አመት 18 በመቶ ጭማሪ መሳየቱን አስረድተዋል፡፡ ለትራፊክ አደጋ ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮች በፍጠነትና አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመፍትሔ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል። በአዲሱ አመት ከልክ በላይ በፍጥነትና አልኮል ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ተሳፋሪውም ተባባሪ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል። ትራፊክ ፖሊስን በመወከል በትምህርት ቤቶች መግቢያና መውጫ ላይ ድጋፍ የሚሰጡ ተማሪዎችን በብዛት ለማሰማራት እቅድ መኖሩን አስረድተዋል። በእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ለህብረተሰቡ የግንዘቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ በፍጥነት በሚጓዝ ተሽከርካሪ በደረሰ የመገልበጥ አደጋ ልጃቸው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባት የተናገሩት የቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃነ ተክሉ ናቸው፡፡ "ትራፊክ ፖሊስ በፍጥነት በሚያሽከረክሩ አሽክርካሪዎች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል" የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። አንዳንድ አሽከርካሪዎችም ከጫኑት ሰው ይልቅ ለሚያገኙት ገንዘብ በማሰብ ስለሚጓዙ አደጋዎች መብዛታቸውን ጠቅሰው ልጃቸው በደረሰበት አደጋ  ቤት ተቀምጦ እንዲውል መገደዱን ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም