የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አመራሩ ራሱን ማብቃት አለበት--አቶ ስዩም መኮንን

155

ጎንደር/ደብረ ብርሀን ሰኔ 1/2014(ኢዜአ) የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በየደረጃው ያለው አመራር በእውቀትና በክህሎት ራሱን ማብቃት እንዳለበት በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ገለጹ፡፡

''አዲስ የፖለቲካ እይታ አዲስ ሀገራዊ እምርታ'' በሚል መሪ ሀሳብ ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጎንደርና በደብረ ብርሀን ከተሞች ማምሻውን ተጀምሯል፡፡

አቶ ስዩም መኮንን እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጥን ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ብቃት ያለው አመራር  መገንባት ያስፈልጋል።

አቶ ስዩም እንዳሉት የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ የሚችል የአመራር አቅምና እውቀት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ አመራሩ ይህን የህዝብ ሃላፊነት በመወጣት በኩል ራሱን በእውቀትና በክህሎት የታገዘ ብቃት እንዲያዳብር አስገንዝበዋል፡፡

''ጎንደር በአመራሩና በህዝቡ የተቀናጀ ጥረት ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡

የጎንደርን መልካም ገጽታ ለማጉደፍ በሃይማኖት ሽፋን ተፈጥሮ የነበረው ግጭት መክሸፉን ገልጸው፤ የህግ ማስከበር ዘመቻውም የሰላም እንቅፋት የሆኑትን በመለየት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማእከላዊ፣ ከሰሜንና ምእራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የዞንና የወረዳ አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው።

በተመሳሳይ ዜና ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፎች እየተሰራ መሆኑን በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ በደብረብረሃን ከተማ በተጀመረው ስልጠና  መክፈቻ ላይ እንዳሉት  የህዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የህግ ማስከበር ጥያቄዎች ለመመለስ የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው።

ህዝብ የሚያነሳቸውን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ ፓርቲው በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር የህዝብን ጥያቄዎች ተቀብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን ለተግብራዊነቱ ቀን ከሌት የሚተጋ እንዲሆን የአቅም ማጎልበት ስራ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ የአቅም ግንባታ ስልጠናም በእውቀት፣ በአመለካከት የተለወጠ አመራር ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም