በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ500 ሚሊዮን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተዋል

4

ሰኔ 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ500 ሚሊዮን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኃሳብ አመንጭነት “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ኃሳብ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተካሂዷል።

በዚህም በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማድረግ ተችሏል።  

የዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል።  

የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መርኃ ግብሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ያስችላል።

ይህም ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አንስተው ላለፉት ሦስት  ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ተመናምኖ የነበረው የተፈጥሮ ኃብት እንዲያገግም መደረጉን ገልጸዋል።  

መርኃ ግብሩ የተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ እንደ አንድ አጀንዳ ሆኖ በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሁን በመላው አገሪቱ ያሉት የችግኝ ጣቢያዎችም 120 ሺህ መድረሳቸውን ገልጸው ይህም በሥራ ፈጠራ ረገድ በርካታ የሥራ እድልን መፍጠር የቻለ ነው ብለዋል።    

በዘንድሮው በአራተኛው ዙር የአረንዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ500 ሚሊዮን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።  

አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና አፕል በዋናነት ለምግብነት ከሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በዘንድሮው የችግኝ ተከላ የሚተከሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።   

እነዚህ ችግኞች በቀጣዮቹ ዓመታት እራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።

ወቅቱ ለችግኝ ተከላ ምቹ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አደፍርስ ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ያሳየውን መነቃቃት እንዲደግመው ጠይቀዋል።

ችግኞች ከተተከሉ በኋላ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳቡት።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።