የ”ቡሳ ጎኖፋ” የንቅናቄ መድረክ በጅማ ተካሄደ

9

ጅማ፣ ሰኔ 1/2014 ( ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም የመረዳዳት ባህል የሆነው የ”ቡሳ ጎኖፋ” የንቅናቄ መድረክ በጅማ ከተማ ተካሄደ።

ቡሳ ጎኖፋ ከገዳ ስርዓት የተቀዳ፣ በችግር ጊዜ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ሲሆን ለአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑም ትናንት በጅማ ከተማ በነበረው የንቅናቄ መድረክ ተገልጿል።

በንቅናቄ መድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በብልጽግና ጽህፈት ቤት የጅማ ከተማ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዋሲሁን ግርማ ቡሳ ጎኖፋ በአዋጅ ቁጥር 244/2014 በጨፌ ኦሮሚያ የተቋቋመና መረዳዳትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የዜግነት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተቋማዊ ሆኖ  በአዋጅ ተቋቁሞ የበለጠ የበጎ ስራ እንዲጎለብት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት በጅማ ከተማ ያሉ ተቋማትና ነዋሪዎች በ17ቱም ቀበሌዎች በክረምቱ መስራት ያለባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በእቅድ ተለይቶ ለየቀበሌዎቹ የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

በጅማ ከተማ በሁሉም ቀበሌዎች በዚህ ክረምት አዲስ 125 ቤቶች ይሰራሉ፣ 131 ቤት የፈረሰባቸው አቅመ ደካሞች ደግሞ ቤታቸው ይታደስላቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በክረምቱ የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴ 2 ሺህ 640 ሰዎች በምግብና ቁሳቁስ የሚደገፉ ሲሆን ከ3ሺህ ዩኒት በላይ ደም ይለገሳል፣ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞችም እንደሚተከሉ ተገልጿል።

ከነዋሪዎችም በተጨማሪ ተቋማትም በበጎ ፍቃድ ስራው 131 ቤቶችን ይሰራሉ፣ 6ሺህ ወገኖችን በምግብና በቁሳቁስ ይደግፋሉ፣ 2ሺህ 800 ዩኒት ደም ይለግሳሉ ተብሎ በእቅድ ተይዟል።

የጅማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን ጆቢር በዚሁ ወቅት እንዳሉት በከተማው ያሉ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ይደረግላቸዋል፣ ስርዓቱም ተቋማዊ በሆነ መልኩ በጎ ስራን የሚያበረታታ በመሆኑም ለመተግበር እንሰራለን ብለዋል።

ቡሳ ጎኖፋ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈታ፣ ለድንገተኛ አደጋ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥና የአረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር የሚሰራ የህዝብ ተቋም ነውም ብለዋል።

ሁሉንም ህብረተሰብ፣ የመንግስት ተቋማትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ ሲሆን ተሳታፊዎች በገንዘብ በጉልበት በአይነት ሊደግፋ እንደሚችሉም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ሼህ አህመድ መሀሙድ “ሀሳቡ የሚደገፍና የተቸገረን ለመርዳት በመሆኑ ለትግበራዊነቱ ሁላችንም እንተባበራለን ብለዋል።

“በሀይማኖታችንም የተቸገረን መርዳት የተወደደ ስራ ስለሆነ አቅም ያለው ደካማውን ሲረዳ ያለው የሌለውን ሲደግፍ ችግር ይፈታል” ብለዋል።

አባ ገዳ ሼህ ነኢም አባ መጫ በበኩላቸው “መደጋገፍ ባህላችን ሆኖ የኖረ ሀብታችን ነው፤ በተደራጀ መንገድ መሆኑ ደግሞ የበለጠ የሚደገፍ ተግባር ነው” ብለዋል።

ስለዚህ በተገለጸው ደረጃ ተተግብሮ ወገኖች ተደግፈው ከችግር እንዲወጡ ቤት የሌላቸው ቤት ተሰርቶላቸው የፈረሰባቸው ታድሶላቸው እንድናይ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ቡሳ ጎኖፋ መላውን የክልሉን ህዝብ እንዲያሳትፍ በቅርቡ በክልሉ መንግስት ደረጃ የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ መከናወኑ ይታወሳል።