የፌዴራል መንግስት የ2015 ረቂቅ በጀት ለአገር ደህንነት፣ እዳ ክፍያ፣ ሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ስራዎች ትኩረት ሰጥቷል

5

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ የፌደራል መንግስት የ2015 ረቂቅ በጀት ለአገር ደህንነት፣ እዳ ክፍያ፣ ሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ስራዎች ትኩረት መስጠቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በረቂቅ በጀቱ 36 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰውን የዋጋ ንረት ወደ 11 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል።


መንግስት ለ2015 በጀት ዓመት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት አዘጋጅቷል፤ በ2014 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትን ጨምሮ ከነበረው የ16 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አለው።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የተያዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 218 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለካፒታል በጀት ተመድቧል፡፡

345 ነጥብ1 ቢሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፤ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ደግሞ ለክልል መንግስታት ድጋፍ እንደሚከፋፈልም አብራርተዋል፡፡

ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ነው ያሉት፡፡

በ2015 የፌደራል መንግስት ጠቅላላ ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 477 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚሆን መታቀዱን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ምንጭ የሚሰበሰበው ገቢ 92 በመቶውን ድርሻ ይይዛል ነው ያሉት።

በጀቱ የቀጣዩን ዓመት ማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ መሰረት ማድረጉን ጠቅሰው፤ በተለይም በቀጣዮቹ ዓመታት በሀገሪቱ ጦርነት ቆሞ፣ ሰላም እንደሚሰፍንና ኢኮኖሚውን መልሶ በመገንባት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ታሳቢ ተደርጎ  መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዓመት ኢኮኖሚው በማገገም የ9 ነጥብ 32 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብም በበጀት እቅዱ ታሳቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የዋጋ ንረት ለበጀት ዝግጅቱ እንደ ግብዓት መወሰዱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት የአጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ በሚያዚያ ወር መጨረሻ 36 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት አስፈላጊ የፖሊሲና መዋቅራዊ እርምጃ ተግባራዊ በማድረግ የዋጋ ንረቱን ወደ 11 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ግብ መያዙን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የገቢ እቃዎች እድገት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት የ18 በመቶ ወደ  በ10 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡

እሴት ታክስ ህግ ማሻሻያ፣ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ እና የንብረት ታክስ ህግ እንደሚተገበሩ በማድረግ የመንግስትን ገቢ ለመጨመር እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

በ2015 በጀት ዓመትና በቀጣዮቹ ዓመታት መንግስት የፊስካል ጫናን ለማቃለልና ጤናማነቱን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በዚህም የመንግስት የወጪ ትኩረት በእዳ ክፍያ፣ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በመልሶ ግንባታና የሀገር ደህንነትን በየማስጠበቅ አቅምን በማጠናከር ላይ ይሆናል ነው ያሉት።

የአፈር ማዳበሪያና የስንዴ ድጎማም ትልቅ ትኩረት እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል።

ለክልሎች የሚደረገው የዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪ በጀት የተጀመሩ አግሮ አንዱስትሪ ፕሮጀክቶችና አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናነቀቅ ላይ ያተኩራል ብለዋል።

በመሆኑም መደበኛ በጀቱን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንደሚመራና የካፒታል በጀቱ ደግሞ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት 231 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉድለት ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ መገመቱንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም በጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 3 ነጥብ 4 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፤ የበጀት ጉድለቱን ከሀገር ውስጥ 224 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ እንዲሁም ከውጭ ሀገር 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የተጣራ ብድር መውሰድ ለመሸፈን መታቀዱን አንስተዋል።

ሆኖም የዋጋ ንረትን ለማርገብ ሲባል ብድሩ በተቻለ መጠን ከመንግስት ግምጃ ቤት ሽያጭ እንዲሚወሰድና ሌሎች ጠንካራ እርምጃዎች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል።

የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት ለማሳካት በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በጀቱን በኃላፊነት እንዲሁም ቁጠባን መሰረት በማድረግ መጠቀም እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ምክር ቤቱ በረቂቅ በጀቱ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ወደ ፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።