አዲሱ ዓመት እጅ ለእጅ ተያይዘን አገር የምንገነባበት መሆን አለበት-ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

62
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 የኢትዮጵያዊያን መሰባሰብ ለሰላም ለፍቅርና ለጋራ ልማት መሆኑን አምነን አዲሱን አመት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ የምንሰራበት መሆን አለበት ሲሉ ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዘዳንቱ አዲሱን ዓመት አስመልክተው የመልካም ምኞት መግለጫ ሲሰጡ "ቀጣዩ ዓመት በአብሮነትና በአንድ ዓላማ አገራችንን የምንገነባበትና የህዝብን ጥቅም የምናረጋግጥበት ነው" ብለዋል። ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ሀዝብ በጋራ በመቆም በዘር፣በብሄርና በሃይማኖት ሳይከፋፈል ካለፈው የስራ ዘመን በመማር  በሰላም፣በልማትና አንድነት ላይ ትልቅ ዋጋ መስጠት ይገባናል ሲሉም ገልፀዋል። በተለይም ባለፉት አራት ወራት የታየው አገራዊ ለውጥ በፖለቲካ ምክንያት ተራርቀው የነበሩ ዜጎች ተገናኝተው በአንድ ጠረጴዛ ላይ እንዲመክሩ ማድረጉ "ለቀጣዩ የልማት ጉዞም ትልቅ ስንቅ ነው" ሲሉም ተናግረዋል። "ኢትዮጵያ ሁሉም ልጆቿ በአንድ ላይ ተሰብስበው ማየት ትፈልጋለች" ያሉት ፕሬዘዳንቱ ቀጣዩ የለውጥ ጉዞ የአንዱ ወገን በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን ከሚደረግ ፉክክርና ሽኩቻ የፀዳ መሆን እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ህዝብን አስቆጥተው የነበሩ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና መሰል ጥያቄዎች መልስ ለማግኘትና ህዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚቻልበት መስመር ውስጥ እንደሚገቡ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላልም ብለዋል። አዲሱ ዓመት የሰላም ፣የፍቅርና የብልፅግና ይሁንላችሁ ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም