በሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ 25 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ ክትባት ይሰጣል

3

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ በሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ 25 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ ክትባት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሦስተኛው ዙር የኮቪድ ክትባት ከሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመላ የአገሪቱ ክፍል ይሰጣል ተብሏል።

በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና የተሰጣቸው ፋይዘር፣ አስትራ ዜንካ፣ ሲኖፋርምና ጆንሰን ጆንሰን የተሰኙ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶች በዘመቻው እንደሚቀርቡ ተገልጿል።   

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የሕጻናት ጤና ዳይሬክተር ዮሃንስ ላቀው እንደገለፁት በሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19  ክትባት ዘመቻ 25 ሚሊየን ዶዝ ክትባት ይሰጣል።

ክትባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚወስዱ፣ አንድ ጊዜ ተከትበው ለሁለተኛ ጊዜ የሚወስዱና ማጠናከሪያ ክትባት ለሚወስዱት ሰዎች የሚቀርብ መሆኑን ነው የገለጹት።

እስካሁን በነበረው የክትባት ዘመቻ 24 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ክትባቱን መውሰዳቸውን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 21 ነጥብ 5 ሚሊየኑ ሙሉ ለሙሉ ክትባታቸውን ወስደዋል ብለዋል።  

አሁን ላይ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ምጣኔ 44 በመቶ መድረሱን ገልጸው፤ የሦስተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ሲጠናቀቅ ይህ አሃዝ ከ60 በመቶ በላይ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።

የክትባት ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን በተለይም ከትምህርት ዘርፉ፣ ከኃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግና የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቱን እንዲወስዱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡም የኮቪድ-19 ክትባት በመውሰድ ለበሽታው የሚኖረውን ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።