የቡሳ ጎኖፋን ስርዓት በማጠናከር የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህል ለማጎልበት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ተባለ

4

ጎባ ግንቦት 30/2014(ኢዜአ)— የገዳ ስርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ባህል የሆነውን የቡሳ ጎኖፋ ስርዓት በማጠናከር የህዝቡ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህል ለማጎልበት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በሁለቱ የባሌ ዞኖች ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የተሰኘ የንቅናቄ መድረክ ትናንትናና ዛሬ ተካሂደዋል፡፡

የንቅናቄው ዓላማ የህዝቡን ጥንታዊ የመረዳዳት ባህል ይበልጥ በማጎልበትና ተቋማዊ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ትብብር መፍጠር መሆኑም ተገልጿል።

በባሌ ዞን ዛሬ በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ እንዳሉት “ቡሳ ጎኖፋ የኦሮሞ ህዝብ ጥንታዊ የመረዳጃና የገዳ ስርዓት አስተምህሮት አካል ነው”።

የክልሉ መንግስት የኦሮሞን ሕዝብ የሚያጠናክሩና የሚጠቅሙ እሴቶች ሕጋዊነት ኖሯቸው እንዲተገበሩ በአዋጅ አጽድቆ ተግባራዊ እያደረጋቸው ከሚገኙ ሀገር በቀል እሴቶች መካከል ቡሳ ጎኖፋ አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የቡሳ ጎኖፋ ስርዓት በችግር ወቅት ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት ተራማጅ እሳቤና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

በተለይ ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ በዞኑ ባገጠመው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህዝቡ በመረዳዳት ያደረገው ተሳትፎ “የቡሳ ጎኖፋ እሳቤ አካል ነው”፤ ያሉት ደግሞ የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሼቱ በቀለ ናቸው፡፡

የንቅናቄው ዓላማም ለዘመናት የነበረውን የህዝቡን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ ለማጎልበትና ተቋማዊ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ መሆኑንም አቶ እሼቱ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ውጤት የሆኑ ጠንካራ እሴቶችን እንዲጠቀምባቸው የክልሉ መንግስት አቅዶ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶች እንዲሰምሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የስርዓቱ ተሳታፊ በመሆን ሊደግፉ እንደሚገባም አቶ እሼቱ ጠይቀዋል፡፡

‘ቡሳ ጎኖፋ’ በአዋጅ ተቋቁሞ  እንዲደራጅ መደረጉ  በተበታተነ መልኩ በህዝቡ ሲደረግ የነበረውን የመረዳዳት ባህል ሕዝቡ ሌሎችን ሳይጠብቅ በራሱ መንገድ ከችግሩ እንዲወጣ የሚያደርግ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን የቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ ናቸው፡፡

ሕዝቡ  በድርቅ ምክንያት የመጣውን ክፉ ጊዜ በቀደመው የ‘ቡሳ ጎኖፋ’ ባሕሉ መሰረት ተረዳድቶና ተደጋግፎ እንዲያልፈው መደረጉ የዚሁ ጥረት አካል ነው ያሉት አቶ ወንድማገኝ፤ አስተምህሮቱ ተቋማዊ እንዲሆንና የህዝቡ የመረዳዳት ባህል ይበልጥ እንዲዳብር ሁሉም ሊያግዝ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪ አባ ገዳ አልይ መሐመድ ሱሩር እንዳሉት ስርዓቱ የኦሮሞ ህዝብ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ ችግር ሲያጋጥመው ችግሩን ለማለፍ የሚታገዝበት ጥንታዊ ባህል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ሊደግፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በባሌ ህዝብ ዘንድ አንድ ሰው ሲቸገር ቁጭ ብሎ በመወያየትና የሚያስፈልገውን ሁሉ በማዋጣት መርዳትና መደገፍ የተለመደ እንደሆነ ያነሱት ደግሞ በባሌ ዞን መድረክ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌ ኡመር አህመድ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት ይህን የቆየ የመረዳዳት ባህል ተቋማዊ እንዲሆን እየሰራ የሚገኘው ተግባር የሚያስመሰግነው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ጨፌ ኦሮሚያ ”ቡሳ ጎኖፋ” የገዳ ስርአት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ስርዓት ነው በማለት በአዋጅ ሲያጸድቅ፣ የክልሉ መንግስትም በክልሉ ያለው ዜጋ በሙሉ እንዲሳተፍበት የንቅናቄ መድረክ ማካሄዱም ይታወሳል።