በጎባ ከተማ የበዓል ገበያን ለማረጋጋት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው

80
ጎባ ጳግሜ 5/2010 በባሌ ዞን ጎባ ከተማና አካባቢዋ የዘመን መለወጫ   በዓል ገበያ ላይ በአንዳንድ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ኢዜአ  ያነጋገራቸው ሸማቾችና ሻጮች ገለጹ፡፡ የከተማው የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ  የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡ ከሸማቾች መካከል አቶ ከበደ ተረፋ እንዳሉት የአዲስ ዓመት መግቢያ በዓል ገበያ በተወሰኑ እቃዎችና የእርድ ከብቶች ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ትልቅ ሰንጋ በሬ ከስምንት እስከ 18ሺህ ብር ሲሸጥ መታዘባቸውን ጠቁመው ይህም ባለፈው ሳምንት ከነበረው ዋጋ ጋር  ሲነፃፀር የተጋነነ  ጭማሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶሮ በመግዛት ላይ ከነበሩት ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ሙንተሃ ሁሴን በበኩላቸው የዶሮ ዋጋ አነስተኛው 130፣  መካከለኛው 200 ፣ ከፍተኛው ደግሞ እስከ 400 ብር እና እንቁላል ደግሞ በ4 ብር  መሸጡን ገልጸዋል፡፡ የዶሮ ዋጋ ከወትሮው እስከ 50 ብር የሚደርስ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቀሱት ወይዘሮዋ የጭማሪውም ምክንያት ከተጠቃሚው ፍላጎት መጨመር ጋር የሚያያዝ እንጂ በአቅርቦት ላይ ችግር እንደሚያመሰላቸው አስረድተዋል፡፡ የእህል ዋጋ ከአምና የበዓላት ገበያ ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ ገበያ በአቅረቦት ደረጃ የተሻለና  መጠነኛ ቅናሽ የታየበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በእህል ንግድ የተሰማሩ አቶ አደም ሀሰን  ናቸው፡፡ "የእህል ዋጋ የተጋነነ ጭማሪ ያልተየበት ምክንያት በቅርቡ የበልጉ አዝመራ ምርት በመሰብሰቡ የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ ነው "ብሏል፡፡ በከተማው የቅቤ ነጋዴው  አቶ ጀማል መሐመድ የአንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ ዋጋ  200 ብር፣ የበሰል ደግሞ 230 ብር በኪሎ ግራም በመሸጥ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከአምና ገበያ ጋር ስነጻጸር የ20 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ የከተማው የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉነህ መንግስቴ እንደተናገሩት የበዓል ገበያው ሰላማዊና የአቅርቦት ችግር የሌለበት ነው፡፡ "ከፍላጎት መጨመር ጋር ተያይዞ በተወሰኑ  እቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም ከወቅቱ የገዥና ሻጭ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ነው እንጂ የተጋነና ሆኖ አለገኘነውም "ብሏል፡፡ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ህገ ወጥ  የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የገበያ ማረጋጋት ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡ ተገቢ ያልሆነ የበዓል ወጪዎችን በመቀነስ የቁጠባ ባህልን በማዳበር አዲሱን ዓመት በፍቅርና በደስታ እንዲያሳልፍ መልዕክታቸውን አስተላልፏል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም