ለሰላም  ዘብ በመቆም  ለተጀመረው  ለውጥ መሪ  ተዋናይ እንሆናለን-  ወጣቶች

65
ጳጉሜ 5/2010 ለሰላም ዘብ በመቆም የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት  ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ወጣቶች አረጋገጡ፡፡ ወጣት ኡርጌሳ ሳጃንካ  በወጣቱ ትግል  በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጾ ከአሁን በኋላ ውጤቱ ለፍሬ የሚበቃው ድንጋይ በመወርወር ሳይሆን ጥያቄዎቹን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በማቅረብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ወጣቱ እንዳለው  “ዲሚክራሲ  በጉልበት ስለማይመጣ  ብጥብጥ  ከመፍጠር  ይልቅ  ችግሮችን   በወይይት  መፍታትን መልመድ” ይገባል፡፡ ወጣቱ የመከፋፈልና  የጥላቻን  ስሜት አስወግዶ  አንድነቱንና ሕብረብሔራዊነቱን ማጎልበት ለሚቻልባቸው አማራጮች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ነው ያስገነዘበው፡፡ ወጣቱ በስሜታዊነት ከሚፈፅማቸው ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት በመቆጠብ  ለውጡን ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት የሰላም ኃይል ሆኖ ሊቀጥል ይገባልም ብሏል፡፡ ወጣት ጋሻው ቢልልኝ እንዳለው ደግሞ  ወጣቱ ኃይል በስሜታዊነት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለሀገርም ለወገንም ስለማይበጁ መደመርን  ከወሬ በዘለለ  በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ለውጡ  ዘለቄታ እንዲኖረውና  የአንድነት መንፈስ እንዲጎለብት ከተፈለገ  ያለፈውን  ዘመን  ቁርሾ  በይቅርታ  ሽሮ ወደፊት መራመድ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገረው፡፡ “ስንደግፍና  ስንቃቀወም  ምክንያታዊ መሆን ይኖርብናል”  ያለው ወጣት ጋሻው ወጣቱ በአሉቧልታና ወሬ ከመጠመድ ይልቅ  ፊቱን ወደ ልማት ማዞር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚናፈሱ ጥላቻ አዘል መልዕክቶችን በጥንቃቄ መመልከት እንደሚያስፈልግ ያስገነዘበው ወጣት ጋሻው ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር በማሸነፍ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር እንደደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ ሌላኛዋ  አስተያየት  ሰጪ ዘሪቱ ወርዳ  እንዳለችው ሁሉም ህብረተሰብ ተስፋ የጣለበት ለውጥ ለፍሬ እንዲበቃ ወጣቱ በግንባር ቀደምነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በአዲሱ ዓመት  የተጀመረውን  የፍቅር፣  የደመርና  የይቅርታ መንፈስ   በማጠናከር  ለለውጥ መትጋት ይኖርብናልም  ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም