የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ፓርኮችና ጥብቅ ደኖችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

2

ደሴ፣ ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፓርኮችና ጥብቅ ደኖች ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመከላከል የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የዓለም የአካባቢ ቀን “አካባቢን በመጠበቅ ምድርን እናሥቀጥል” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ሣይንት ወረሂመኑ ብሄራዊ ፓርክ አክብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ሃላፊ አቶ በልእስቲ ፈጠነ እንደገለፁት፤ በክልሉ ያሉ ስድስት ፓርኮችና አምስት ጥብቅ ደኖች ልቅ ግጦሽ፣ ህገ ወጥ እንስሳት አደን፣ ደን ምንጠራ፣ ህገ ወጥ ከሰል፣ የእርሻ መስፋፋትና ሌሎች ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል።

ችግሩን ለማቃለል የሰው ሃይል በማደራጀት ጽህፈት ቤትና ሎጅ እንዲኖራቸው በማድረግ እንዲጠበቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ አካባቢን በመጠበቅና የደን ሽፋኑንም በማሳደግ የአካባቢን ለውጥና ብክለትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሁሉም እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካባቢው ያለውን ጥብቅ ደንና ፓርክ በመጠበቅ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።

በፓርኮችና ጥብቅ ደኖች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በመፍታት እንዲለሙና እንዲጠበቁ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሃመድ አበጋዝ በበኩላቸው በተለያየ ምክንያት ጥብቅ ደኖችና ፓርኮች ለምተው በሚፈለገው ልክ ለቱሪዝም አገልግሎት ሊበቁ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ፓርኮቹና ጥብቅ ደኖቹ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ስራ ጀምረናል ብለዋል።

ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍነው የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንተነህ ተስፋዬ ፓርኩ ከአመራሩና ህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተን ጥበቃና ልማት ጀምረናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ