በጉጂ ዞን በመስኖ ከለማው መሬት 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ምርት ተሰበሰበ

87
ነገሌ ግንቦት 10/ 2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበጋ ወራት በመስኖ ከለማው መሬት 3 ሚሊዮን 920 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ የኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ቦሩ ገልገሎ እንደገለጹት በዞኑ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 30 ሺህ 855 ሄክታር መሬት በፍራፍሬ፣ አትክልትና በቆሎ ለምቷል። በልማቱም በዞኑ 14 ወረዳዎች የሚገኙ 69 ሺህ 283 አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በዘንድሮው የበጋ ወራት በባህላዊ መስኖ ልማት የተገኘው የምርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ895 ሺህ 127 ኩንታል ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡ አቶ ቦሩ እንዳሉት፣  በዞኑ የመስኖ ልማት አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እያደገ መምጣት እንዲሁም ተጨማሪ 1 ሺህ 838 ሄክታር አዲስ መሬት እንዲለማ መደረጉ ለምርቱ መጨመር ምክንያት ናቸው። በዞኑ በባህላዊ መስኖ ከለማው መሬት ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ በቆሎ፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ጎመን፣ ካሮትና ቀይስር የመሳሰሉ ይገኙበታል ። በዞኑ ሊበን ወረዳ የኮባዲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሁሴን የሱፍ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት  ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ለተጨማሪ ገቢ በባህላዊ መስኖ በቆሎና ሽንኩርት ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ አመት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የበቆሎ ሰብል 20 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውንና ለእንስሳት መኖ የሚሆን ተረፈ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ መስኖ አለመኖር፣ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ እንዲሁም የተባይ መከላከያ መድኃኒት ችግር የሚፈለገውን ያክል ምርታማ ለመሆን እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በሁለት ሄክታር መሬት ላይ 300 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመሰብሰብ ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ሊበን ወረዳ የለጋ ጉላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ክፍሌ ሙሉነህ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ዙር መስኖ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ገልጸው በመንግስት በኩል ምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ግብአት በወቅቱ የማቅረብ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ቦሩ ገልገሎ በበኩላቸው በአርሶአደሮች እየተነሳ ያለው የግብአት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ባለስልጣኑ ከሚለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገገር ላይ መሆኑን አስታውቋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ በተጎዳውና በአመዛኙ አርብቶ አደር ማህበረሰብ በሚገኝበት ጉጂ ዞን በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን ከቡድን መሪው ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም