የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተሞች የውሃ ችግር እንዲፈታ የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ ጠየቀ

246

ግንቦት 26/2014(ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 12 ዓመታትን የዘገየው የቦንጋ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥያቄ አቀረበ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ የተመራ ልዑክ በክልሉ የሚካሄዱ  የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ተመልክቷል፤ ከክልሉ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ለልዑኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ሕዝብ ቅሬታ እያነሳ ነው።  

በክልሉ በስፋት ቅሬታ ከሚነሳባቸው ከተሞች መካከልም የክልሉ ጊዚያዊ ዋና ከተማ ቦንጋ፣ የዳውሮ ዞን ዋና ከተማ ተርጫና የሸካ ዞን ዋና ከተማ ማሻ ይገኙበታል ብለዋል።

በተለይም የቦንጋ ከተማ የከርሰ ምድር ውሃ ለከተማዋ ተደራሽ ለማድረግ ከ12 ዓመት በፊት የግንባታ ቁፋሮ ቢጀመርም እስካሁን ምንም ሥራ አለመሰራቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የሕዝብ ቁጥሩ እያደገ የመጣው የቦንጋ ከተማ በውስጡ ለሚገኙ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ውሃ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የውሃና መብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ባልሆነችው ማሻ ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ለጨረታ 50 ሚሊዮን ብር በጀት ቢያዝም የጨረታ ዋጋ ከ318 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኗል ብለዋል።

በዙሪያው በርካታ የውሃ ሃብቶችን የያዘውና ከክልሉ ክላስተር ከተሞች አንዱ የሆነው የተርጫ ከተማም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የውሃ ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።

የፌዴራል መንግሥት በጀት ማፈላለግ፣ በሌሎች መርሃ ግብሮች እንዲታቀፉ በማድረግም ሆነ በሌሎች አማራጮች እነዚህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ አንዲሆኑ ድጋፍ ጠይቀዋል።

አዲሱ ክልል መሰረታዊ ወጪዎችን እንኳን በቅጡ የሚሸፍን ሃብት እንዳልፈጠረ ገልጸው፤ የዓመታት ቁልፍ ጥያቄ የሆነው የቦንጋ ከተማና የሌሎችም ከተሞች መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መፍትሔ ይሻል ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላችው አገሪቷ ከገጠማት ጦርነትና ተያያዥ ችግሮች አኳያ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመር አልተቻለም።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ውስጥ በውጭ ምንዛሬ ሳቢያ የዋጋን ንረት እንደገጠማችው አስታውሰዋል።

ሚኒስቴሩ በተገኙ ዕድሎች በውሃ ዕጦት ለተቸገሩ የክልሉ ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች ለማስጀመር የበኩሉን ሚና ይወጣል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚመለከታቸው አካላት በሃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ በውሃ ማከሚያ ኬሚካል አቅርቦት፣ በአቅም ግንባታ ድጋፍና በውሃ ልማት ፕሮግራሞች ክፍፍል ረገድም ፍትሃዊነት ባረጋገጠ አግባብ እንዲፈጸም የሚጠበቅበትን  ሚና ይወጣል ብለዋል።

በክልሉ ያጋጠሙ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮችን ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ለመስጠትም ከክልሉ ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ክልሉ በንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦት 39 በመቶ የውሃ ሽፋን ሲኖረው ከነዚህም መካከል በገጠር 36 ነጥብ 8 በመቶ፣ በከተማ 41 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም