የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሴራሊዮን አቻውን አሸነፈ

72
ሀዋሳ ጳጉሜ4/2010 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን   ለአፍሪካ  ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም የሴራሊዮን አቻውን አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸነፈ፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎሉን ያስቆጠረው በ35ኛ ደቂቃ  በፍፁም ቅጣት ምት በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ነው፡፡ ዋልያዎቹ በተረጋጋ አካሄድ ማጥቃትን መሠረት ያደረገ ጨዋታ ተከትለው ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃ ጌታነህ የሳተው ጎል የሚያስቆጭ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ባይችሉም ከእረፍት መልስ በርካታ ተጫዋቾችን የቀየሩት የሴራሊዮኑ አሰልጣኝ በአንፃራዊነት የተሻለ ኳስ መጫወት ችለዋል፡፡ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አቶ አብርሃም መብራቱ ቡድናቸው ማሸነፍ በመቻሉ በምድቡ ውስጥ እኩል ተፎካካሪ በመሆኑ  መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአጨራረስ ብቃት ማነስ በስተቀር ቡድኑ በጨዋታው ብልጫ እንደነበረው ያመለከቱት አሰልጣኝ አብርሃም ወደ ቀጣይ ዙር  በማለፋቸው በተጫዋቾቻቸው መኩራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሴራሊዮን አሰልጣኝ ጆን ክርስቲያን  እንዳሉትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ለማሸነፍ ችለዋል፡፡ ጨዋታውን በተመለከተ ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው ገልጸው " ከዋልያዎቹ ጋር የተጫወትኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበረ አስቸጋሪ ነበረ ማሸነፍ ይገባቸዋል "ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም