"ፎርተስኪው ፊዩቸር ኢንዱስትሪስ’ በማዕድን ዘርፍ ልማት ለመሰማራት የሚያስችለውን የኢንቨስትመንት ፈቃድ አገኘ

92

ግንቦት 26/2014 (ኢዜአ)‘ፎርተስኪው ፊዩቸር ኢንዱስትሪስ’ የተሰኘው የአውስትራሊያ የማዕድን ኩባንያ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ለመሰማራት የሚያስችለውን የኢንቨስትመንት ፈቃድ አገኘ።

ኩባንያው የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተከትሎ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ጥናት በቅርቡ እንደሚያካሂድ ትላንት ማምሻውን በአዲስ አበባ በተካሄደው መርኃ ግብር ገልጿል።  

ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የታዳሽ ኃይል ኃብት በመጠቀም በካይ ጋዝ የሚለቁ የነዳጅ ምርትን የሚተካ የካርበን ልቀት የሌለው አረንጓዴ ሃይድሮጅንና አሞኒያ ልማት ላይ እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።

ኩባንያው የሚያመርተው አረንጓዴ ሃይድሮጅንና አሞኒያ (ነዳጅ) ለተለያዩ ከፍተኛ ነዳጅ ኃይል ለሚጠቀሙ ኩባንያዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ባቡሮችና ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ግብዓትነት ይውላል ተብሏል።

የፎርትስኪው ፊዩቸር ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጁሊ ሸትልዎርዝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ለመሰማራት ከዓመት በላይ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

ይህንንም ተከትሎ ኩባንያው ፍቃድ ማግኘቱን ገልጸው፤ ኩባንያው ከባቢ አየርን በማይጎዳ መልኩ በቅርቡ  ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን ተግባራት እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።

ኩባንያው በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በስፋት በመሰማራት ኩባንያው በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

በዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ነው ያሉት።      

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ኩባንያው በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሰረተ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል።

በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን በመደገፍና በዘርፉ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአረንጓዴ ልማት እምብረት እንድትሆን ኩባንያው አስተዋጽዖ የጎላ ነው ብለዋል።   

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ሃይድሮጅንና አሞኒያ ልማት ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ኩባንያዎችና ተሽከርካሪዎች፣ ባቡሮች፣ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የሚለውን ነዳጅ ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚ በሆነ አቻ ምርት ለመተካት ያስችላል ብለዋል።  

ይህም ለኢትዮጵያ ገበያ ብቻ ሳይሆን አገሪቱ በቀጣይ ለአውሮፓ ገበያ ምርቱን ለማቅረብ የሚያስችላት መደላድል በመፍጠር ረገድ ትልጅ ጅማሮ መሆኑንም ነው ያነሱት።      

መንግሥት ለኩባንያው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኩንያው ሥራውን በፍጥነት እንዲጀምር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።  

ፎርተስኪው ፊዩቸር ኢንዱስትሪስ ኩባንያ እ.አ.አ በ2003 የተቋቋመ ሲሆን፤ ኩባንያው በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ የሚሰራ ሥመ-ጥር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም