ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዞኑ ከ43ሺህ ቶን በላይ ቡና ለምርት ገበያ ቀረበ

95

ግምቢ፣ ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ43ሺህ ቶን በላይ ቡና ለምርት ገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በጽህፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን እንደገለጹት በዞኑ ቡናን በተሻለ በማምረት አርሶ አደሩ የልፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ቡና ያምርት እንጂ የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበር ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም፣ አሁን ግን ምርቱን በቀጥታ ወደ ምርት ገበያ ማቅረብ በመጀመሩ የተሻለ ዋጋ እያገኘ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በዞኑ ቡና ከአርሶ አደሩ ገዝተው ለምርት ገበያ የሚያቀርቡ 982 ነጋዴዎች፣ 4 የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖችና 2 ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

በእነዚህና በአርሶ አደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 43 ሺህ 407 ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለምርት ገበያ መቅረቡንም አመልክተዋል።

አምና በተመሳሳይ ወቅት 38 ሺህ 927 ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለምርት ገበያ የቀረበ  ሲሆን የዘንድሮው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በ4ሺህ 480 ቶን ብልጫ አንዳለውም አብራርተዋል፡፡

በግምቢ ከተማ የቡና ነጋዴ የሆኑት አቶ ኑረዲን መሐመድ ከአርሶ አደሩ ቡናን በመግዛት ለምርት ገበያ ያቀርባሉ።

ከዚህ ቀደም ቡናን ወደ ምርት ገበያ ሲያቀርቡ በምርት ገበያው ውስጥ ባለው የአሰራርና ኪራይ ሰብሰቢነት ችግር ምክንያት የቡና ዋጋ ዝቅ ሲደረግባቸው እንደነበርና ለኪሳራ ሲዳርጋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ባለው የተሻሻለ አሰራር አርሶ አደሩም ሆነ ነጋዴው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡

በላሎ አሰቢ ወረዳ የላሊሳ ላሎ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ጂሬኛ ዳበሳ በማህበራቸው አማካይነት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለምርት ገበያ በማቅረብ ማህበሩ ተጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አክለውም በወረዳው ዘንድሮ ምቹ የአየር ሁኔታ በመኖሩ የተሻለ የቡና ምርት መገኘቱንና በቂ የቡና ምርት ለምርት ገበያ እያቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የግምቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ኩመራ ጃለታ በበኩላቸው ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ ቡና ቢያመርትም የልፋቱን ዋጋ እንደማያገኝና ዛሬ ጥሩ ዋጋ እያገኙ መሆኑን አብራረተዋል፡፡

ዘንደሮ ካመረቱት ቡና 19 ኩንታል እንዳገኙና በመጪው ክረምት በሩብ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ  የቡና ተክሎችን በአዲስ ለመተካት፣ በሩብ ሔክታር ላይ ደግሞ አዲስ የቡና ችግኝ ለመትከል እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በቡና ከተሸፈነው 489 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት 70 በመቶ  ምርት እየሰጠ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም