የእርስ በእርስ ግጭት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን ቤተ-ክርስቲያኗ የአስታራቂነት ሚናዋን ለመወጣት ትሰራለች

12

ግንቦት 25/2014( ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእርስ በእርስ ግጭት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን የአስታራቂነት ሚናዋን እንደምትወጣ ገለጸች።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሐይማኖት አባቶች ለአገር አንድነትና ሰላም  እንዲሰሩም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጠይቋል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ በየዓመቱ በግንቦት ወር የሚያካሒደውን ርክበ ካሕናት ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቅዱስ ሲኖዶሱ ለ16 ቀናት ሲያካሒድ የነበረውን ዓመታዊ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ አገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ባካሔደው ውይይት በአገሪቱ ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ተወግዶ ዘላቂ ሰላም በሚሰፍንበት ጉዳይ ላይ መምከሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ግጭት ተወግዶ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ቤተ- ክርስትያኗ የአስታራቂነት ሚናዋን ትወጣለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

ጉባኤው በቤተክርስቲያኗ እና ምእመናን ላይ እየደረሱ ባሉ ችግሮች ላይ የተወያየ ሲሆን መንግስት ተከታትሎ አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለአገር አንድትና ሰላም  እንዲሰሩም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ ማቅረቡን ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ገልፀዋል።

በጉባኤው  መንፈሳዊ አገልግሎት በሚጠናከርበት፣ የአገር አንድነትና የህዝቦች ሰላም በሚጎለብትበት፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው በሚመለሱበትና በመላው  ዓለም ሰላም ለማስፈን መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ተመክሯል።

በመሆኑም መላው ሕዝብና የመንግስት አካላት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ከምንግዜውም በላይ  በጋራ እንስራ በማለት የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን አቅርቧል።