በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ታሪክ የሃይሌ ገብረስላሴ አይበገሬነት እኔን ለጠንካራ ተፎካካሪነት አብቅቶኛል – አትሌት ፖል ቴርጋት

4

ግንቦት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ታሪክ የሃይሌ ገብረስላሴ አይበገሬነት እኔን ለጠንካራ ተፎካካሪነት አብቅቶኛል” ሲል ታዋቂው ኬንያዊ አትሌት ፖል ቴርጋት ተናገረ።

የዓለማችን ድንቁ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ እና ኬንያዊው ታዋቂ አትሌት ፖል ቴርጋት የበዛ ወዳጅነት ያላቸው መሆናቸው ይነገራል።

የሁለቱ አትሌቶች ወዳጅነት የሚታወቅ ቢሆንም ለውድድር አንድ ላይ ሲሰለፉ ግን ሩጫው የከረረ፣ አሸናፊነቱ ለድል አድራጊው ፈንጠዝያ፤ ለተሸናፊው ደግሞ ከሐሞት የመረረ መሆኑን ይናገራሉ።

በረዥም ርቀት ሩጫ 27 የዓለም ክብረ ወሰኖችን የሰባበረው ጀግናው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ እንደ ቴር ጋት አይነት ጠንካራ ተፎካካሪዎች ቢኖሩትም እርሱ እያለ አልፎ ክሯን መበጠስ አይሞከርም።

በረዥም ርቀት ውድድር የሃይሌ ተፎካካሪ ከነበሩ ስመ-ገናና አትሌቶች መካከል የሚጠቀሰው አትሌት ፖል ቴርጋት ሃይሌን በውድድር ማሸነፍ ሲያቅተው ጀርባውን በቡጢ የመታበትን አጋጣሚም ብዙዎች አይረሱትም።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው ቴርጋት በዓለም አትሌቲክስ የውድድር አጋጣሚዎች ከሃይሌ ጋር የነበሩትን እልህ አስጨራሽ ፉክክሮች አሁንም ያስታውሳቸዋል።

“በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር ታሪክ ሃይሌን የመሰለ አትሌት ባይኖር ኖሮ እኔ ይህን ያክል የአትሌቲክስ ጠንካራ ተፎካካሪ እሆን ነበር ብዬ አላስብም” ይላል ቴርጋት።

በአትሌቲክስ መድረክ የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር ከአሸናፊነት ባለፈ ለዘርፉ እድገት ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑን ይናገራል።

የሁለቱ አገራት የረዥም ርቀት ሩጫ አይረሴ ፉክክሮች አሁንም መቀጠላቸውን ጠቅሶ ፉክክሩ በአሸናፊነት ለመወጣት ጠንክረው እንዲሰሩ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጿል።

“ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቴ ናት” የሚለው አትሌቱ የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች እርስ በርስ ተፎካካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ ወዳጆችም ናቸው ብሏል።

የሁለቱ አገራት አትሌቶች ተፎካክረው ክሩን ከበጠሱ በኋላ በመተቃቀፍ “እንኳን ደስ ያለህ!” በመባባል በወዳጅነት የሚተሳሰቡ መሆኑን ፖል ቴርጋት ይናገራል።

የሁለቱ አገራት ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞች በአሸናፊነታቸው በሚያገኙት ገንዘብ ለአገሮቻቸው ያበረከቱት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ጠቅሷል።

የአትሌቶቹ አስተዋጽኦ ከኢኮሚያዊ ጠቀሜታም ባለፈ በቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንት እና ሌሎችም መስኮች የማይደበዝዝ አሻራቸውን እያኖሩ መሆኑን ገልጿል።

የዓለምን የረዥም ርቀት ውድድር የተቆጣጠሩት የሁለቱ አገራት አትሌቶች አስደናቂ ስኬት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።