በአማራ ክልል የራስን ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

73
ባህርዳር ጳግሜ 4/2010 በአማራ ክልል ሰላምን በማወክ  የራስን ፍላጎት ለማሳካት በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አሳሰበ። ቢሮው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች  ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ የራስን ፍላጎት ለማሳካት የዝርፊያ፣የንብረት ማውደምና የመንግስት ኃላፊነትን የተሸከሙ አካላትን የሚጋፉ ህገወጥ ተግባራት እየተካሄዱ ነው፡፡ በህዝብ መስዋትነት የመጣውን ሰላም ያልተመቻቸው፣  ጥቅማቸው ካለመረጋጋትና ብጥብጥ ጋር የተገናኘ ጸረ-ሰላም ኃይሎች  ባለፉት ጊዜያት  ተፈጥረው የነበሩ ቀውሶች  እንዲመለሱና  የለውጡ መሰናክል ለመሆን እየሰሩ ይገኛሉ። የክልሉ የጸጥታ ኃይል ዳግም የሰው ህይወት እንዳይጠፋና የአካል ጉዳት እንዳይደረስ  በከፍተኛ ትግስት እራሱ እየደማና እየሞተ የህዝቡን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ይገኛል። ሆኖም ይህ እርምጃ ባንድም ይሁን በሌላ ጥቅማቸው የሚነካ የመሰላቸውና ውስጣቸው ለሰላም፣ለይቅር ባይነት፣ለአንድነትና ለፍቅር መገዛት ሽንፈት መስሎ የታያቸው ኃይሎች መሆኑ ተደርሶበታል ሲል በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የለውጡን ጉዞ ከመላው ህዝብ ስሜትና  አመለካከት በላይ  እኛ እናውቃለን በሚል  ሴራ ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ግርግር እንዲቀጥልና የሰው ህይወት  እንዲጠፋ እየተሰራ ነው። ለህዝብ ለህዝብ ለማጋጨት የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በመልቀቅና  ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ  መውተርተር በስፋት ይታያል ሲል ቢሮው በመግለጫው አስታውቋል። በተሳሳተ መረጃና አሉቧልታ  በመነዳት በተለይ ለውጡንና የህግ የበላይነትን በህገ-ወጥ መንገድ ለማስፈጸምና መንግስትን ተክቶ ለመስራት  እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የክልሉ ኢኮኖሚ የጀርባ እጥንት የሆነውን  የግብርና ምርት እንዳይሸጥና  የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዳይሻሻል ከፍተኛ ጫና እንዳለ ያመለከተው የቢሮው መግለጫ የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡ በክልሉ የልማትና የኢንቨስትመንት ተቋማት ፣በአርሶ አደር ተመርተው ለገበያ የቀረቡ  የተለያዩ ምርቶች ላይ የሚደረግ ቅሚያና ሀገር አቋራጭ የጭነት  ተሽከርካሪዎን ማገትና ጉዳት ማድረስ፣ የክልሉን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ድርጊቶች በመሆኑ የጸጥታ ኃይሉ ህግን የማስገበር ስራ ላይ እንደማይደራደር  ነው የተገለጸው። ህዝቡ ይህንን ተረድቶ ነጻነቱን ጠብቆ ለመቀጠል በዚህ ተግባር የተሰማሩ  አካላትን ሊከላከላቸው እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡ የክልሉን  ሰላምና መረጋጋት  በማወክ  የራስን ፍላጎት ለማሳካት በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም  የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ በመግለጫው አሳስቧል። የክልሉ ህዝብ   ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ በመስዋትነት የተገኘውን ሰላም ማስቀጠል እንደሚገባውም ቢሮው ጥሪውን አስተላልፋል፡፡                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም