በአዲስ አበባና በክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የሥነ ዜጋ ትምህርት ለመስጠት ታቅዷል

117

ግንቦት 24/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባና በክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የሥነ ዜጋ ትምህርት ለመስጠት መታቀዱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ የሥነ ዜጋ ትምህርትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለዜጎች ማስተማር ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር አካሂዷል።

በምክክሩ ላይ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የህግ ባለሙያዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።     

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ዶክተር አበራ ደገፋ፤ መራጩ ህዝብ መብትና ግዴታ ላይ እውቀት እንዲኖረው የሥነ ዜጋ ትምህርት በቋሚነት ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለይ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገኙ እድሜያቸው ለመምረጥ የደረሱ ተማሪዎችን በአዲስ አበባና በክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የሥነ ዜጋ ትምህርት ለመስጠት እቅድ መኖሩን ጠቅሰዋል።   

የሚሰጠው ትምህርት ከመደበኛው የስነ ዜጋ ትምህርት ጋር የሚጋጭ እንዳልሆነም አብራርተዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም ሲቪክ ማህበረሰቡ ስነ ዜጋ ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ምን ዓይነት ተሳትፎ ይኖራቸዋል? በቀጣይስ ከቦርዱ ጋር እንዴት በቅንጅት መስራት ይችላሉ የሚለውን ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል።  

በምክክር መድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀሩቡት የህግ ባለሙያው ደበበ ኃይለገብርኤል፤ የሥነ ዜጋ ትምህርትን ማስፋፋት ለአንድ አገር የዴሞክራሲ መጎልበት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።

ዜጎች መብታቸው ምን ድረስ ነው?፣ በአገራቸው ጉዳይ የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲሁም የፖለቲካ መብቶችን በማስገንዘብ ረገድም ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት።  

የሥነ ዜጋ ትምህርት የበርካታ አካላትን ተሳትፎ የሚሻ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርስተዎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተደራሽነቱ ረገድ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።  

የስነ ዜጋ ትምህርት ለተማሪዎች ብቻም ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች ለጎልማሶችም እንዲሰጥ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።  

የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ተቋማትም የሥነ ዜጋ ትምህርትን ተደራሽነት ማስፋፋት ላይ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፤ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የታየው የህዝብ ተሳትፎ ውጤቱ የስነ ዜጋ ትምህርት መሆኑን ገልጸዋል።   

በመሆኑም የሲቪል ማህበራት ከምርጫ በዘለለ በቋሚነት ለዜጎች ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም