የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ ነው

226

ግንቦት 24/2014/ኢዜአ/ የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን የተለያዩ ላኪ ድርጅቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል።

በመሆኑም በዚህ ደርጅት በኩል የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ላኪዎች ገልጸዋል።

የኤ ኤን ኤች ኢንፖርት ኤክስፖርት የኦፕሬሽን ሃላፊ ፍሰሃ ባራኪ፤ የተለያዩ የቅባት እህሎችን ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት መላክ ከጀመሩ አምስት ዓመታት መሆኑን ይናገራሉ።

ለገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት አስፈትሸው መላክ ከጀመሩ በኋላ የጥራት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

ምርቶቻቸውን ቀደም ሲል ወደ ቻይናና ቱርክ ይልኩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ወደ ህንድና አረብ ሀገራት ጭምር በመላክ ምርቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል።

ምርቶቻቸውን ሳያስፈትሹ በመላክ እንዲመለስና ተቀባይነት እንዲያጣ ችግር የሚፈጥሩ አንዳንድ ላኪዎች በመኖራቸው ተገቢው ክትትል እንዲደረግባቸው ጠይቀዋል።

በመሆኑም ላኪ ድርጅቶች የተፈተሸና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በመላክ ለራሳቸውም ይሁን ለአገር ጥቅም እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ድርጅት የውጪ ንግድ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ምስጋና እሸቴ፤ በሶስት አገሮች ብቻ የጀመሩት የውጭ ገበያ አድማሱን አስፍቶ ወደ 10 ሀገራት ማደጉን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፍተሻ ማድረጋቸው ደግሞ የውጭ ገበያ መዳረሻቸውን ማስፋቱን ጠቁመው ሌሎች ላኪዎችም ተመሳሳይ አሰራር እንዲከተሉ መክረዋል፡፡

ምርቶችን እሴት ጨምሮ፣ ጥራት ጠብቆ እና ደረጃቸውን አሟልቶ መላክ ለአገርም ለራስም ጥቅም የሚያስገኝ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቤል አንበርብር፤ ምርቶቻቸውን አስፈትሸው የሚልኩ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የተሰማሩ ላኪ ድርጅቶች የሚሰጠውን ምዘና በማለፍ ሁሉም ላኪዎች ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም