የጀርመኑ ሲመንስ የህክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ 10 የአልትራሳውንድ ማሽኖችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ

6

ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ)  የጀርመኑ ሲመንስ የህክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ 10 የአልትራሳውንድ ማሽኖችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ ፡፡

የርክክብ መርሃ-ግብሩ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተካሄደ ሲሆን፤ ማሽኖቹንም በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየር ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ አስረክበዋል፡፡

ኩባንያው 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጡን እነዚህን ማሽኖች ያበረከተው በጀርመን የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ  አስተባባሪነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየር በዚህን ወቅት ጀርመን በኢትዮጵያ የጤና ስርዓትን ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ አስታውቋል፡፡

በዚህም ጀርመን በተለይ የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማቶችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት እየደገፈች መሆኑን አንስተው፤ በዛሬው እለት የተደረገውን ድጋፍም በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተዋል፡፡  

የጀርመን መንግሥት ድጋፉን ያደረገው ከግሉ ሴክተር ጋር ባለው አጋርነት አመካኝነት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ድጋፉን ያደረገው ድርጅት በቀጣይ የቴክኒክ ስልጠና ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት፡፡

የአልትራሳውንድ ማሽኖቹ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመመርመር እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው የልማት አጋሮች የሚያደርጉት ድጋፍ ኢትዮጵያ በሽታን ለመከላከል ለየምታደርገውን ድጋፍ በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የዛሬው ድጋፍም ሆስፒታሎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝንና ሌሎች በሽታዎችን ለማከም የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

ለተደረገው ድጋፍም በሚኒስቴሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡