የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

156

ሀረር (ኢዜአ) ግንቦት 23/2014 የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት በኢትዮጵያ የጋራ እሴቶች ላይ አተኩሮ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በሀረር ከተማ ታካሂዷል።

መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የጋራ እሴቶች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም እንደገለጹት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ድርሻቸው የላቀ ነው።

በሀገሪቱ ያሉትን በጎ የሰላም እሴቶች ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ለዘላቂ ሰላም ጠንክረው እንዲሰሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን በዘመናት የተከማቹና የተገነቡ መልካም እሴቶች ባለቤት በመሆናቸው የህብረተሰቡን አብሮነት አጽንቶ ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በሃይማኖት ሽፋን የህዝቡ የአብሮነት እሴቶች እንዲሸረሸሩ የሚሰሩ መሰናክሎችን በማለፍ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የማስተማር ስራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢው ትውልድ የትላንትና የአብሮነት ታሪኩን በአግባቡ እንዲያውቅ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኋላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው የኢትዮጵያዊያንን የጋራ እሴቶች ማወቅ፣ ማበልፀግና መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በሀገሪቱ ያሉ በርካታ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ተጠንተው ባለመሰናዳታቸው በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻሉን ተናግረዋል።

ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች መኖራቸውን የገለጹት ሃላፊው፣  እሴቶቹን ማወቅ፣ ማልማትና በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የህግ ባለሙያው አቶ ቀለመወርቅ ሚደቅሳ እንዳሉት በዘር በሃይማኖትና በቋንቋ ልዩነቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያዊያን በሀገር ጉዳይ በአንድነት እንደሚቆሙ ከጥንት ጀምሮ የተረጋገጠ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራ የእርስ በርስ ግንኙነት ያለውና በጠላት ሴራ የማይከፋፈል  በመሆኑ የጋራ እሴቱን በማጎልበት አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እርስ በርሱ የተዋለደና የተጋመደን ህዝብ በቀላሉ መከፋፈል እንደማይቻልም ጠቁመዋል።

"ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላት ሲመጣ አንድ ሆነው በተባበረ ክንዳቸው የጠላትን ትንኮሳ የመከቱ ጥበበኛና ብልህ ህዝቦች ናቸው" ያሉት ሌላው ጽሁፍ አቅራቢ ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ ናቸው።

"ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን የሚያስታርቁ የበርካታ እሴቶች ባለቤት በመሆናችን ይህንን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል" ሲሉም አክለዋል።

በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የሐረሪ ክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም