ማህበሩ በጂንካና አካባቢዋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

94

ጂንካ፤ ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ)፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጂንካ ከተማና አከባቢዋ ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ ካሁን በፊት በአራት ዙሮች ለተፈናቃዮች ድጋፍ አድርጓል።

 የተደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ለአምስተኛ ዙር  240 ሺህ  ብር ግምት ያላቸውን ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን 1 ሚሊዬን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለምግብነት የሚውሉ ግብአቶች የተካተቱበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ከማህበሩ አባላትና ከግለሰቦች በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ማህበሩ ለእለት ጉርስ ከሚሆኑ ድጋፎች በተጨማሪ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገውን ጥረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግለሰቦችና ተቋማት በዕለት ደራሽ ምግቦችና በመልሶ ማቋቋሙ ስራ ላይ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ የሴቶችና ህፃናት መብትና ደንብ የማስጠበቅ ዳይሬክተር ቡድን መሪ አቶ ጨቡድ ሙሉነህ በበኩላቸው በአከባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ከ1 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውስጥ  53 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሴቶችና ህፃናት ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን አመልክተው፤ መምሪያው ከሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስቸኳይ የምግብና ሌሎች የቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው ተጎጂዎች መካከል የቶልታ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰኢድ አራጌ  የእሳት አደጋው በንብረታቸው ላይ ውድመት  ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች ባደረጉላቸው የተለያዩ ድጋፎች መፅናናታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ተፈናቃይ ወይዘሮ መሪሟ ሰኢድ በበኩላቸው የጂንካ ማህበረሰብ፣የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

 ''የቀድሞው ሰላማችንን ለመመለስ ማህበራዊ ትስስሩን ማጠናከር ይገባል'' ያሉት ወይዘሮ መሪሟ፤በወንጀሉ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ።

ከሚያዚያ 1/2014 ጀምሮ በጂንካና አከባቢዋ ተከስቶ በነበረው ግጭት ከ147 በላይ መኖሪያ ቤቶች በእሳት የወደሙ ሲሆን ከ1 ሺ በላይ ተጎጂዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም