የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት፤ የአህጉሩን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል

66

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት፤ የአህጉሩን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን እና የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት በቀጣዩ ዓመት ህዳር በአዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ወጣቶች ወር በማስመልከት ተወያይተዋል።

የውይይታቸውም ትኩረት በፌዴሬሽኑ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በማስመልከት ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ጽጌሬዳ ዘውዱ፤ ፌዴሬሽኑን የፋይናንስና የሰው ሃይል እጥረት እንዲሁም የድጋፍ ማነስ እየፈተነው መሆኑን ገልፃለች።

ይህም ሆኖ ፌደሬሽኑ በአካባቢ ጥበቃና በደን ልማት፣ በፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ፣ በበጎ ፈቃደኝነትና ሌሎችም ተግባራት ጥሩ አፈፃፀም ማሳየቱን ተናግራለች።

ከፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት ጋር የተደረገው ምክክር ተሞክሮዎችን በመጋራት የአህጉሩን ወጣቶች ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ጠቁማለች።

በውይይቱም በቀጣይም በትብብር ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንቷ ጠቅሳለች።

የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ወር በአዲስ አበባ የሚያከበር መሆኑን አስታውሳ በጉዳዩ ላይ መምከራቸውንም ተናግራለች።

የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት ዋና ጸኃፊ ቤኒንግ አህመድ ዊስቾንግ፤ ህብረቱ የአፍሪካ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከወጣት ፌደሬሽኖች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን የተለያዩ ማነቆዎች አጋጥመውት እያከናወነ ያለውን የግባር በማድነቅ በቀጣይ አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጧል።

የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት፤ የአህጉሩን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል ብሏል።

የኢትዮጵ ወጣቶች ፌዴሬሽን የወጣቶችን ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ በሚል በ2001 ዓ.ም መመስረቱ ይታወቃል።