የአብሮነት እሴት እንዲሸረሸሩ የጥቂቶች የሚፈጽሙትን እኩይ ተግባር ማምከን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት መሁን አለበት --- የሀገር ሽማግሌዎች

173

ሚዛን አማን ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ) ለሰላም መሠረት የሆኑ የአብሮነት እሴት እንዲሸረሸሩ የጥቂቶች የሚፈጽሙትን እኩይ ተግባር ማምከን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

ዘመናትን ያስቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ መስተጋብሮች ትግል ፋላጎታቸውን ለማሳካት በሚሰሩና ያልተገባ የፖለቲካ ጥቅም ለማትረፍ በሚሰሩ አካላት እንዳይሸረሸር መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ከካፋ ዞን ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ወርቁ ወልደማርያም እንዳሉት ባህላዊ የአብሮነት እሴቶች ሀገራዊ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ነው።

"በየአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሚና የሚጫወተው የአብሮነት እሴት እንዳይሸረሸር መጠበቅና የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማረም ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል" ብለዋል።

አቶ ወርቁ እንዳሉት የቀድሞ አባቶች ችግሮች ሲፈጠሩ ሌላ ቀውስ ከመፍጠራቸው በፊት በባህላዊ መንገድ በመዳኘት የህዝቡን አንድነትና ሰላም ሲያስጠብቁ ቆይተዋል።

"ግጭት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ወደጥላቻና ሁከት እንዳያድግ በእንጭጩ የማክሰም ባህል አለን" ያሉት የሀገር ሽማግሌው ዛሬ ላይ ትንንሽ ችግሮችን ለማስፋት የሚጥሩ አካላት በየአካባቢው እንደሚታዩ ተናግረዋል።

አብዛኛው ማህበረሰብ የአብሮነት እሴት ሚዛኑን ጠብቆ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለይ በአብሮነት በሚኖረው ህብረተሰበ ውስጥ የጥቂቶች እኩይ ምግባር ቦታ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል።

"ሰላማችንን በመከባበርና በእርቀ ሰላም እሴቶቻችን መጠበቅ እንችላለን" ያሉት አቶ ወርቁ በካፈቾ ብሔረሰብ "ቃብትኖ" የሚባለው ባህላዊ ዳኝነት በየአካባቢው ሰላምን ለማጽናት እንደሚተገበር ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሸካ ዞን የማሻ ወረዳ ሀገር ሽማግሌ አቶ ተሰማ ጋሎ በአካባቢያቸው ከሁሉም ጋር በፍቅርና በሰላም ለመኖር የሚያስችሉ በርካታ ባህላዊ መሠረቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት "ወራፎ" የሚባል እሴት መኖሩን ገልጸው፣ ሥርዓቱ ሰዎች ባሉበት አንድነታቸውን አጠንክረው በሰላም እንዲኖሩ የሚያስችልና አጥፊም የሚጋለጥበት መሆኑን ገልጸዋል።

"ያለሰላም ምንም ነገር ማድረግ ሰለማይቻል የሀገር ሽማግሌዎች ችግሮችን ፈጥነን በእርቅ የመፍታት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

ወጣቶች ኢትዮጵያዊነታችን የተመሠረተበትን ጠንካራና መልካም እሴት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል የግንዛቤን ሥራ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ከትላንቱ መልካም ነገሮችን በመውሰድ ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ አንድነትና ህብረትን ማጎልበት እንደሚገባም የሀገር ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም