በኢሉባቦር ዞን 84 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጁ

213

መቱ ግንቦት 23/2014/ኢዜአ/በኢሉባቦር ዞን በክረምቱ ወራት 84 ሚሊዮን የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት ለተከላ የተዘጋጁት የቡና ችግኝ በአዲስ መሬት ላይ የሚተከሉና ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል የሚተኩ ናቸው።

ለተከላ ከተዘጋጁት የቡና ችግኝ መካከል ከ40 ሚሊዮን የሚበልጡት ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል የሚተኩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ በ7 ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ያረጁ የቡና ተክሎችን ነቅሎ በአዲስ የቡና ችግኝ ለመተካት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አቶ ቻላቸው ተናግረዋል።

በመጪው ክረምት በዞኑ በሚካሄደው የቡና ችግሽ ተከላ ከ17 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።

በዞኑ ወደ 257ሺህ ሔክታር መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት በ185 ሺህ 500 ሔክታር ላይ የሚገኘው የቡና ተክል ምርት እየሰጠ ነው ብለዋል።

በዞኑ በዚህ ዓመት ከ128 ሺህ 520 ቶን የሚበልጥ የቡና ምርት  መገኘቱን አቶ ቻላቸው አስታውቀዋል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች አርሶ አደሮች በክረምቱ ለሚተክሉት የቡና ችግኝ የዝግጅት ስራ አጠናቀው የተከላ ወቅት እየተጠባበቁ መሆናቸው ገልፀዋል።

የመቱ ወረዳ አርሶ አደሮች አቶ ታከለ ዲቤሳ በመጪው ክረምት በአዲስ መሬትና ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል ለመትከል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኘውን ያረጀ ቡና ነቅለው በአዲስ በመተካት ካለሙት ቡና ዘንድሮ ከሶስት ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የአሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ታረቀኝ ባልቻ በዚህ ዓመት ከ1 ሺህ 700 በላይ የቡና ችግኞችን ለመትከል ቦታ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ታረቀኝ አክለውም ካላቸው ሁለት ሔክታር የቡና ማሳ በዚህ ዓመት ሩብ ያህሉን በመንቀል በአዲስ ችግኝ ለመተካት እየሰሩ መሆናቸውም ገልጸዋል።

በዚህ ለቡና ችግኝ ተከላ ዝግጅትም የባለሙያ ምክርና የሙያ ድጋፍ እንዳልተለያቸው አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል።

ያረጁ የቡና ተክሎችን ነቅሎ የማደሱን ስራ ቀደም ሲል እምብዛም እንደማያምኑበት የገለጹት አቶ ዓለማየሁ አረጋ ናቸው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የቆዩ የቡና ተክሎች ምርት እየቀነሱ በመምጣታቸው አሁን ያረጁ የቡና ተክሎችን ነቅለው በአዲስ ወደ መተካት ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

 ከሁለት ሔክታር በላይ በቡና የለማ መሬት ያላቸው ሲሆን በዚህ ዓመት ያገኙት የቡና ምርት አራት ኩንታል መሆኑን አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል።