ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

97

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማበረታታት የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ሠላምይሁን አደፍርስ እንደገለጹት፤ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ነው።      

አሁን ላይ ደግሞ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ኢንተርፕራይዝ መሆን እንዲችሉ ማበረታቻዎችን የያዘ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው አዋጁ ለመጽደቅ የሚያስችሉ አስፈላጊው ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።          

አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎችን ለመደገፍ ሚኒስቴሩ እያወዳደረ መሆኑን ጠቁመው ተወዳድረው ያሸነፉ ፈጣሪዎች የገንዘብ፣ የቴክኒክና የሥልጠና ድጋፎችን እያገኙ መሆኑን አብራርተዋል።    

የልማት አጋሮች አሸናፊ ለሆኑ ኃሳቦች ገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።     

ለአብነትም በተያዘው ዓመት 97 ለሚሆኑ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ ተወዳድረው ላሸነፉ 50 የፈጠራ ባለቤቶች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።       

በሶፍትዌር ማበልጸግ ላይ የሚሰሩ ሰባት የፈጠራ ባለቤቶች እየተደገፉ መሆኑን ነው ጠቁመዋል።

የኮሪያው ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ ጋር በተመባበር ተወዳድረው ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ከ1 ሺህ እስከ 3 ሺህ ዶላር ድረስ መበርከቱንም አክለዋል።   

ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ጃይካ/ በመሆንም አክሲለሬተር በተሰኘ መርኃ ግብር ዙሪያ ድጋፎች የሚደረጉበት አሰራረር መዘርጋቱንም አስረድተዋል።     

ኢኖቬሽን ለልማት ፕሮጀክት በሚል መርኃ ግብርም ከቀድሞው ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመሆን 10 የፈጠራ ባለኃሳቦች ተመርጠው የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አብራርተዋል።   

ሚኒስቴሩ አዳዲስ የፈጠራ ኃሳብ ያላቸውን ልጆች ከመደገፍ ባሻገር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆችም የሚያወጡበት ሥርዓት እየዘረጋ ነው።

የተለየ ተሰጥኦ ኖሯቸው በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ሊስተናገዱ የማይችሉ ልጆች ለብቻቸው ተለይተው ተሰጧቸውን የሚያዳብሩበት ትምህርት ቤት በቀጣዩ ዓመት ሥራ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም