በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የትንባሆ ንግድ ቁጥጥርና ማስወገድ ፕሮቶኮልን ለማጽደቅ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

75

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የትንባሆ ንግድ ቁጥጥርና ማስወገድ ፕሮቶኮልን ለማጽደቅ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ የምግብና መድሃኒት ጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ በትንባሆ ጭስ ምክንያት በዓመት 17 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡም ነው የተጠቆመው፡፡

የፀረ ትንባሆ ቀን “ትምባሆ ለእኛና ለምድራችን ስጋት ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም ለ35ተኛ  በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ  ዛሬ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ የምግብና መድሃኒት ጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ቀኑን በመዲናዋ በከተማ ደረጃ  አክብሯል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት በዳዳ ቀኑን በማስመልከት በመዲናዋ 11ዱም ክፍለ ከተሞችና በስምንት አደባባዮች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በትንባሆ ጭስ ምክንያት በዓመት 17 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ በቅርቡ የተጠና አንድ ጥናት ማመላከቱንም ነው የተናገሩት፡፡

ትንባሆ አጫሾች በተለይም በካንሰር ፣ በልብ፣ በሳንባና፣ በጨጓራ ህመም የመሞት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በትንባሆ ስርጭት ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ   የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ሕገ-ወጥ የትንባሆ ንግድ ቁጥጥር ማስወገድ ፕሮቶኮልን ለማጽደቅ የሚከናወነውን ስራ በአብነት አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለዚሁ ተግባር ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ደንብና መመሪያዎች በዝግጅት ላይ ስለመሆናቸውም ነው የገለጹት፡፡

ከፌዴራል የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና ከጉመሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆንም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የትምባሆ ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም እንዲሁ፡፡

የትምባሆ ምርት ይዘትን በመቆጣጠር፤ ስለትንባሆ ጎጂነት ማስታወቂያ በተከታታይ መሥራት፤ሕገ-ወጥ የትንባሆ ንግድ ቁጥጥርን በማጠናከር፤ ከትምባሆ ውጪ አማራጭ የኢኮኖሚ ገቢ ሻጮች እንዲያገኙ ማድረግና ችግሩን የሚቀንሱ ሳይንሳዊ ግኝቶችን በማስፋት የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ እንደሚሰራም   ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትንባሆ ጭስ ምክንያት የሚሙቱ ሲሆን ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ሌሎች በሚያጨሱት የትንባሆ ጭስ ተጎድተው እንደሚሞቱ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።